ኤሚልስ ኩዳ ‘በብዝሃ ህይወት ላይ የሚመክረው የ COP16 ጉባኤ ለሰዎችም ትኩረት መስጠት አለበት' አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከ200 ሀገራት የተውጣጡ ወደ 15,000 የሚጠጉ ልዑካን፣ 140 የመንግስት ሚኒስትሮች እና በደርዘን የሚቆጠሩ ሀገራት መሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ የአገሬው ተወላጆች እና የቤተክርስቲያን ተወካዮች በኮሎምቢያዋ ካሊ ከተማ ‘ኮፕ16’ (COP16) ተብሎ በሚጠራው 16ኛው የተባበሩት መንግስታት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
“ከተፈጥሮ ጋር በሰላም መኖር”
የአየር ንብረትን ዋና ትኩረቱ አድርጎ ከሚካሄደው የኮፕ ጉባኤ ጋር አቻ ግምት የሚሰጠው ይሄኛው የኮፕ16 የመሪዎች ጉባኤ ከጥቅምት 11 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ “ከተፈጥሮ ጋር በሰላም መኖር” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፥ ዋና ትኩረቱንም የምድራችንን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉትን የብዝሀ ህይወት ፈተናዎችን ለመቅረፍ የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማመላከት እንደሆነም ተነግሯል።
የዛሬ ዓመት የዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ጉባዔ በዓለማችን የብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ አዲስ ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ መደረሱ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ ስምምነት የተነገረው የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ሕይወት ሀብት ጉባኤ ወይም COP15 በሞንትሪያል ካናዳ ከመጠናቀቁ ከአንድ ቀን በፊት ሲሆን፥ የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ጉባዔ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት 30 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን የተፈጥሮ መሬት እና ውኃ አካባቢዎች እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2030 ዓ.ም በጥበቃ ስር እንዲሆኑ የሚደነግግ እንደሆነና፥ ስምምነቱ በሺህ የሚቆጠሩ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ዉኃ የሚያገኙባቸው አካባቢዎች በጥበቃ ክልል ዉስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ያቀደ መሆኑ ተገልጿል።
ስነ-ምህዳሮችን ለመጠበቅ እና ዓለም አቀፋዊ የአካባቢ ፖሊሲዎችን ለማጠናከር፣ ብሎም ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማበረታታት በማለም በ2030 የብዝሃ ህይወት መጥፋትን ለማስቆም እና ለመቀልበስ በካናዳ ተካሂዶ በነበረው ኮፕ15 ጉባኤ ወቅት የፀደቀውን የኩሚንግ-ሞንትሪያል ብዝሃ ህይወት ማዕቀፍን (ጂቢኤፍ) ፍኖተ ካርታው አድርጎ የወሰደው ሲሆን፥ “የፓሪስ የብዝሃ ህይወት ስምምነት” ተብሎ የተሰየመው ስምምነት 30 በመቶ የሚሸፍነውን የመሬት እና ባህር አካልን ከአደጋ መከላከል፣ የፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ስጋትን በግማሽ ያክል መቀነስ እና 30 በመቶ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ 23 ግቦችን እንዳካተተ ተገልጿል።
እንደ ጎረጎሳዊያኑ በ 1992 ዓ.ም. በደቡብ አሜሪካዋ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ከተካሄደው የሥነ ምህዳር ጉባኤ በኋላ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረው ይህ ዓለም አቀፋዊ ዝግጅት የተካሄደው በሚቀጥለው ዓመት በብራዚሏ ከተማ ቤለም ከሚደረገው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ኮንፈረንስ ኮፕ30 ጉባኤ (COP30) አንድ ዓመት ሲቀረው እንደሆነ ተነግሯል።
ቤተክርስቲያን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች
ኮሎምቢያ ተወዳዳሪ የሌላት የብዝሀ ሕይወት ሀብት ባለቤት በመሆኗ ጉባኤው በካሊ መደረጉ ጠቃሚ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ ሃገሪቷ በዓለም ላይ ካሉ ስለ ሕገወጥ ማዕድን፣ አንድ ዓይነት ልማዳዊ እርሻን እና የደን መጨፍጨፍን የሚሟገቱ በርካታ የአካባቢ ማኅበራዊ ተሟጋቾች ያሉባት እንደሆነች፣ እንዲሁም ለኑሮ በጣም አደገኛ ከሆኑ ቦታዎች ውስጥ ቀዳሚ እንደሆነች፣ ለአብነትም እ.አ.አ. በ 2023 ብቻ 73 ግድያዎች የተፈጸሙባት ሲሆን፥ ይህም በዓለም ዙሪያ ከሚፈጸሙ ግድያዎች 40 በመቶውን ይይዛል ተብሏል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጋራ ቤታችንን እንድንንከባከብ ላቀረቡልን ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በኮሎምቢያ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስትያን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በንቃት የምትሳተፍ ሲሆን፥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሲቪሉ ማህበረሰብ የዜጎችን በአካባቢያዊ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተሳትፎን ለማጠናከር በሚል ‘ግሪን ዞኖች’ ላይ በሚዘጋጁ በርካታ ክፍት ዝግጅቶች ላይ በንቃት እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
ለጋራ ቤታችን የተደረገ የ ‘ላውዳቶ ሲ’ ጥሪን መጋራት
በጉባኤው ላይ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ከሆኑት ሞንሲኞር ፓውሎ ሩዴሊን ጨምሮ የቫቲካን ባለስልጣናት ልኡካን የተገኙ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ፍጥረትን ስለ መንከባከብ ያስተላለፉትን መልእክት ያጋሩት የላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኤሚልስ ኩዳ የተገኙ ሲሆን፣ ባደረጉት ንግግርም የተገለሉ ሕዝቦች መንግሥታዊ ውሳኔዎች ላይ የመሳተፍ መብት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
የአካባቢያዊ ቀውስ ማህበራዊ ገጽታ እንዲታይ ማድረግ
አርጀንቲናዊቷ የነገረ መለኮት ምሁር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አስተምህሮቶች በሆኑት በላውዳቶ ሲ እና ፍራቴሊ ቱቲ ላይ የተጠቀሱትን እጅግ ወሳኝ የሆኑት የሥነ-ምህዳር ጭብጦች የተዳሰሱበት ጥቅምት 14 ቀን የተካሄደውን “ዓለም አቀፍ የአፍሪካዊያን ፎረም” ን እንዲሁም ኩዌሪዳ አማዞኒያን ጨምሮ በሦስት ዝግጅቶች ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ወይዘሮ ኩዳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአካባቢ እና የብዝሃ ህይወት ቀውስ ማህበራዊ ገጽታ እንዲታይ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀው፥ የካቶሊክ ማህበራዊ አስተምህሮ የእንስሳት እና የእፅዋት ዝርያዎች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ህይወትም እንደሚሟገት፣ ይህ ማለት የአገሬው ተወላጆች እና ትውልደ አፍሪካዊአን ህዝቦች የተፈጥሮ ሃብቶችን አጠቃቀም እና አላግባብ መጠቀምን በሚመለከት የውሳኔ ሰጪው አካል ውስጥ እንዲካተቱ በትጋት ትሰራለች ብለዋል።
የአገሬው ተወላጆችን ማሳተፍ
ወይዘሮ ኩዳ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና ኢኮ-ሲቲዘን በሚባለው ተቋም በጋራ በተዘጋጀው እና የተለያዩ ኃይማኖቶች የብዝሀ ሕይወት እንክብካቤ ላይ በጋራ መስራት በሚችሉበት መንገዶች ላይ ለመወያይት ባለመው የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካን ልማት ባንክ (IDB) እና በኮንሰርቬሽን ኢንተርናሽናል አማካይነት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፥ በስብሰባው ላይ ‘የብዝሃ ህይወት ክሬዲት’ በመሳሰሉ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ መሳሪያዎች በኩል የሃገሬው ተወላጅ እና ትውልደ አፍሪካዊያን ህዝቦች የተፈጥሮ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ በሚቻልበት መንገዶች ላይም ተወያይተዋል።
ወይዘሮ ኩዳ በመጨረሻም እነዚህ ዝግጅቶች ሁለቱንም ስነ-ምህዳሮች እና የሀገር በቀል ባህሎችን ለመጠበቅ የታለሙ የቤተክርስትያን ተነሳሽነቶች ለመደገፍ የሚውል ገንዘብ ለመሰብሰብ በመፍቀዳቸው ጠቃሚ እና ፍሬያማ እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክት ከመንግስታት፣ ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከገንዘብ ተቋማት ጥሩ አቀባበል እንዳገኘ፣ “ቤተክርስቲያኒቱም በዚህ ልትኮራ ይገባታል” ሲሉ ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።