እስራኤል የሊባኖስ ከተማ በሆነችው ጢሮስ ላይ ያደረሰችው ጥቃት   እስራኤል የሊባኖስ ከተማ በሆነችው ጢሮስ ላይ ያደረሰችው ጥቃት   (AFP or licensors)

እስራኤል በሊባኖስ እና በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏ ተነገረ

የእስራኤል ወታደሮች የሊባኖስ ከተማ በሆነችው ጢሮስ ውስጥት እና አከባቢዋ በሚገኙ ህንፃዎች ላይ ሰኞ ዕለት በርካታ ጥቃቶችን የፈጸሙ ሲሆን፥ ተንታኞች እንደሚናገሩት የጢሮስ ከተማ ዋና ኢላማ የሆነችበትን ምክንያት ሲገልጹ ሂዝቦላህን በመወከል ሲደራደር የነበረው የ ‘አማር እንቅስቃሴ’ አመራሮች ምሽግ ነው ተብሎ እስራኤል መረጃ ስለደረሳት ነው ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ አጠናክራ ከቀጠለችው ጥቃት ጎን ለጎን በሊባኖስ በምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ የመከላከያ ሰራዊቷ በሳምንቱ መጨረሻ በሃገሪቷ በሚገኘው ሆስፒታል ላይ ጥቃት ማድረሷ ተነግሯል።

እስራኤል ባለፉት አራት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎች ሊባኖስ ላይ ስታደርስ ቆይታለች። ጥቃቱ የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ እና ቡድኑ የሚጠቀምባቸው መሠረተ ልማቶች እና የጦር መሣሪያዎችን ለማውደም ያለመ ነው ብላለች።

ከመስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስራኤላውያን በጋዛ ሰርጥ ላይ ባደረሱት ጥቃት 43,000 ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የእስራኤል ጦር በአሁኑ ወቅት ሀማስ ድጋሚ ራሱን እያደራጀበት ነው ባለው ሰሜናዊ ጋዛ ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ ሲሆን፥ ባለፉት 24 ሰዓታትም ከ40 በላይ የቡድኑ ታጣቂዎችን ገድያለሁ ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ የፍልስጤም ንፁሀን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ መሆኑን እና ግጭቱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ መስፈርቶችን ወደ ጎን በማለት እየተካሄደ ነው ብሏል።

ባለፉት ቀናት ብቻ በሰሜናዊ ጋዛ ተጠናክሮ በቀጠለ ወታደራዊ ዘመቻ እስራኤል ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎችን በተለይም ሴቶች እና ህጻናትን ገድላለች።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሁድ ዕለት ካደረጉት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት በኋላ ባደረጉት ንግግር በቀጠናው እየተባባሰ ያለው ግጭት እንዲቆም እና ክቡር ለሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ቅድሚያ እንዲሰጠው ባቀረቡት ጸሎት “በየዕለቱ የሚገደሉት ሕጻናት ምስሎች እንደሚያሳየው እጅግ በርካታ ሲቪሉ ህዝብ በግጭቱ የመጀመሪያ ተጠቂ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ቤት-ላህያ ከተማ በሚገኘው ካማል አድዋን ሆስፒታል ላይ ባደረገው ወረራ 44 ወንድ ሰራተኞችን ጨምሮ 100 ተጠርጣሪ የሃማስ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን፥ የዓለም ጤና ድርጅት እና የፍልስጤም የህክምና ባለሙያዎች 200 የሚሆኑ ህሙማንን በማከም ላይ የሚገኘው ሆስፒታሉ ላይ በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል።

እስራኤል 400,000 ፍልስጤማውያን የሚኖሩባትና ወደ ሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል የሚደርሰው ሰብዓዊ ዕርዳታ ባለፈው ወር እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ረሃብ በእጅጉ የተስፋፋባትን ሰሜናዊ ጋዛን ነዋሪዎቹ ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች።

ሞት እና መፈናቀል በሊባኖስ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ብቻ ከ2,600 በላይ ዜጎቿ መገደላቸውን እና 12,200 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጿል።

በሊባኖስ በተካሄደው ጦርነት ከ400,000 በላይ ህጻናትን ጨምሮ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

በጋዛ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኋላ ለአንድ ዓመት ያክል ድንበር አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ የነበሩት እስራኤል እና ሄዝቦላህ ወደለየለት ጦርነት መግባታቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ እስራኤል በተለያዩ የሊባኖስ አካባቢዎች የአየር ጥቃት እና የመሬት ለመሬት ወረራ ጀምራለች።

እስካሁን ከ2500 በላይ ሊባኖሳዊያን መገለዳቸውን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የእስራኤል ባለሥልጣናት ደግሞ በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል 59 ሰዎች መገደላቸውን ገልፀዋል።

የሰላም ድርድርን በተመለከተ ግብጽ በጋዛ የአጭር ጊዜ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን፥ ለአጭር ቀናት በሚደረገው ተኩስ አቁም የተወሰኑ ታጋቾች እና የሀማስ እስረኞች እንዲለቀቁ ተጠይቋል።

ግብፅ አራት እስራኤላውያን የሃማስ ታጋቾችን በተወሰኑ የፍልስጤም እስረኞች ለመለወጥ በጋዛ የሁለት ቀን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን፥ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ይህን ያሉት ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው አስከፊውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር ድጋሚ በተጀመረበት ወቅት ነው።

የ43 ሺህ ንጹሀንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለማስቆም ግብጽ ፣ ኳታር እና አሜሪካ አሁንም የድርድር ጥረታቸውን ቀጥለዋል። አደራዳሪዎቹ አሁን እያቀረቡ የሚገኙት የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት አላማም ከበርካታ የድርድር ሙከራዎች በኋላ ያልተሳካውን ዘላቂ ተኩስ አቁም በጊዜያዊነት በመቀየር ወደ ሚፈለገው የጦርነት ማስቆም ሂደት ለመጓዝ መሆኑ ተዘግቧል።

እስራኤል ግብጽ ባቀረበችው የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ምክረ ሃሳብ ላይ እየተወያየች ሲሆን፥ ሃማስ በበኩሉ እስካሁን ድረስ ለዕቅዱ ግልጽ የሆነ ምላሽ አልሰጠም ተብሏል።

እስራኤል ምንም እንኳን በድርድሮቹ እየተሳተፈች ብትገኝም ሀማስ በጋዛ ያለው የእስራኤል ወታደራዊ ሃይል እና የአስተዳደር አካል እስካልወጣ ድረስ ጦርነቱን ማቆም እንደማይችል ጽኑ አቋም መያዙ የሽምግልና ሂደቶቹ ስኬታማነት ላይ ጥላ ማጥላቱ ተነግሯል።
 

30 October 2024, 13:01