ሊባኖስ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንበት ማስና ከተማ ላይ የደረሰውን የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ ሊባኖስ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንበት ማስና ከተማ ላይ የደረሰውን የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ 

እስራኤል በሊባኖስ ላይ ባደረሰችው ጥቃት የሞቱት ህጻናት ቁጥር መጨመሩ ተነገረ

እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃት ከጀመረች ሁለት ሳምንት ሲሆናት ከቀናት በፊት ደግሞ የእግረኛ ሠራዊቷን አሰማርታ ሊባኖስ ውስጥ ዘመቻ እያካሄደች መሆኑ ተዘግቧል። የእስራኤል ጦር በአስርት ዓመታት ውስጥ ካካሄዳቸው ጥቃቶች እጅግ የከፋውን ጥቃት ሰሞኑን በዌስት ባንክ ካካሄደ በኋላ በቤይሩት እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ቀጥለው ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ ዩኒሴፍ እስራኤል ሂዝቦላን የማጥፋት ዘመቻ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በሊባኖስ የተገደሉት እና የቆሰሉ ህፃናት ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን በማሳሰብ፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የሰብአዊ ዕርዳታ ለማድረስ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪውን አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሊባኖስ የሚገኙ ወደ 900 የሚጠጉ መጠለያዎች ከአሁን በኋላ ከእስራኤል ጥቃት ሸሽተው የሚመጡ ተጨማሪ ሰዎችን የመቀበል አቅማቸው ሙሉ በሙሉ እንደተሟጠጠ ተዘግቧል።

በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት አርብ ዕለት ያወጣው መግለጫ እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ ባካሄደችው ዘመቻ 127 ሕጻናት መገደላቸውን የሚገልጽ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ከ100 በላይ የሚሆኑት ባለፉት 11 ቀናት ውስጥ የተገደሉ እንደሆኑ ያሳወቀ ሲሆን፥ ይህ አኃዝ ምሽቱን ከወላጆቻቸው ጋር ቱልካርም ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ እያሉ የተገደሉትን የሁለት ተጨማሪ ልጆች ሞት እንደማያካትትም ተገልጿል።

በሊባኖስ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ብቻ በተደረጉ ጥቃቶች ከ690 በላይ ህጻናት ጉዳት እንደደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ የህፃናት አድኑ ድርጅት ዩኒሴፍ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡን በመቀጠል፥ ሁሉም አካላት ህጻናትን እና የሲቪል መሠረተ ልማቶችን እንዲጠብቁ እና የሰብአዊ ሥራ ተዋናዮች በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ መሰረት ለተቸገሩት መድረስ እንዲችሉ አሳስቧል።

ባለፉት ሳምንታት በአስገራሚ ሁኔታ እየተባባሰ በመጣው ግጭት ከ400,000 በላይ ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን፣ የጨቅላ ሕፃናት የፅኑ እንክብካቤ ክፍልን ጨምሮ በትንሹ 10 ሆስፒታሎች ላይ ጉዳት መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማል።

በህፃናት ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት
“ይህ አስከፊ ግጭት በልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው” ሲሉ የዩኒሴፍ የክልል ዳይሬክተር አዴል ኮድር ተናግረዋል።

“በስፍራው የሚገኙ ዶክተሮች በደም የጨቀዩ፣ የቆሰሉ እና የተሰበሩ፣ እንዲሁም በአካል እና በአእምሮ የሚሰቃዩ ህጻናትን እንዳከሙ ነግረውናል” ያሉት ዳይሬክተሯ፥ በርካቶች በጭንቀት፣ ካዩት አሰቃቂ ነገር እና ከፍንዳታ ጋር በተያያዙ አደጋዎች ምክንያት በከፍተኛ ቅዠቶች እየተሰቃዩ እንደሆነ እና ማንም ልጅ እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታዎች ሊደርስበት እንደማይገባ ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ሕፃናትም ጭምር በጣም ይሠቃያሉ፥ መቼ ወደ ቤት ወይም ወደ ትምህርት ቤት እንደሚመለሱ ስለማያውቁ የፍርሃት፣ ጭንቀት፣ እና የመረበሽ ስሜት ውስጥ ይገባሉ።

ሃላፊዋ አክለውም በተለይ እነዚህ የጦርነት ክስተቶች በአእምሯዊ ጤንነታቸው ላይ የሚያሳድሩት የረጅም ጊዜ ተጽእኖ እንደሚያሳስባቸው ጠቅሰዋል።

የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ውድመት
የሊባኖስ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የተጎጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኝ እና በግጭቱ ምክንያት በቀጥታ እንደተጎዱ፥ ቢያንስ 10 ሆስፒታሎች በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።

ዩኒሴፍ 100 ቶን የድንገተኛ ህክምና አቅርቦቶችን ወደ አከባቢው ያደረሰ ሲሆን፣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሌላ 40 ቶን እንደሚለግስ ይጠበቃል። እነዚህ አቅርቦቶች በመላው ሊባኖስ ውስጥ ለሚገኙ ሆስፒታሎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ማዕከላት፣ ጊዜያዊ ክሊኒኮች እና የመጀመሪያ ደረጃ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎች እንደተሰራጩ የተነገረ ሲሆን፥ እነዚህ እርዳታዎች ለቤተሰቦች በተለይም ለነፍሰ ጡር ሴቶች እና ህጻናት የህይወት አድን አገልግሎት እንደሚውሉ ተገልጿል።

በሊባኖስ ካለው ከፍተኛ የፍላጎት መጠን አንፃር፣ ዩኒሴፍ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያሰባስብ እና ወደ ሊባኖስ የሚገቡት የአቅርቦት መስመሮች ክፍት መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ በመጠየቅ፣ ይህም ለተቸገሩ ህጻናት የህይወት አድን ዕርዳታን በፍጥነት እና በአስተማማኝ መልኩ ለማድረስ ያስችላል ተብሏል።
 

07 October 2024, 16:03