የሚላን ካቴድራል የሚላን ካቴድራል   (Copyright (c) 2019 muratart/Shutterstock. No use without permission.)

ሚላን የወጣቶች መብት ላይ ያተኮረ ፌስቲቫል እያስተናገደች ትገኛለች

ለወጣቶች ተስማሚ የሆኑ ዝግጅቶችን ያካተተው፥ የህፃናት እና የአዳጊ ልጆች መብቶች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ፌስቲቫል በጣሊያን ከተማ ሚላን ተጀምሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ይህ ፌስቲቫል “እርስዎ ትክክል ነዎት፥ ሚላኖ ለህፃናት፣ ልጃገረዶች እና ታዳጊ ወንዶች መብቶች” በሚል ርዕስ በተከታታይ የሚቀርቡ መስተጋብራዊ ዝግጅቶች ወጣቶችን ስለመብታቸው ለማስተማር ያለመ ነው የተባለ ሲሆን፥ ፌስቲቫሉ ከጥቅምት 12 እስከ 16 ድረስ የኢጣሊያን ከተማ በሆነችው ሚላን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አከባቢዎች እየተከበረ ይገኛል።

በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው ‘ቴሬ ዴስ ሆምስ’ የተባለው ህፃናት አድን ድርጅት ከሚላን ከተማ አስተዳደር የህፃናት እና አዳጊዎች መብት ዋስትና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ነው።

ዝግጅቱ በህፃናት እና ወጣቶች ደህንነት ላይ በማተኮር በእያንዳንዱ ቀን በሚደረጉ ውይይቶች፣ ቲያትራዊ ትርኢቶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች እና ህዝባዊ ዝግጅቶች በኩል ጠቃሚ ጉዳዮችን በማንሳት ለመወያየት ያለመ ዝግጅት እንደሆነም ጭምር አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

የበዓሉ ክስተቶች
ከ 1998 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘው የሪካርዶ ካቴላ ፋውንዴሽን ማክሰኞ ዕለት የንግድ ሥራዎች ሚና እና ለመጪው ትውልድ ዘላቂነት ያለው የወደፊት ሁኔታን በመቅረጽ ረገድ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለውን አቅም በማሳየት የመክፈቻውን ዝግጅት ያሰናዳ ሲሆን፥ ዋና ትኩረቱ ዘላቂነት ያለው ባህልን በማሳደግ በተለይም በትምህርት እና በማህበራዊ ተሳትፎ ወጣቶች ማብቃት ላይ እንደነበር ተገልጿል።

ረቡዕ ዕለት የነበረው የፌስቲቫሉ መርሃግብር በመብቶች እና በወጣቶች ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ስብሰባ በማድረግ ሲሆን፥ “ጉስቁልና እና የወጣቶች ድህነት፡ የቤኔሜሪቲ ቁርጠኝነት እና የስፓዚዮ ኢንዲፌዛ ምሳሌ በሚላን” በሚል ርዕስ ውይይት ተካሂዶ ነበር። ከተሰብሳቢዎቹም ውስጥ የሚላን ህፃናት እና ታዳጊ ልጆች መብቶች ጥበቃ ቢሮ አቶ ሲልቪዮ ፕሪሞሊ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ እና ለአደጋ የተጋለጡ ቡድኖች ጥበቃ የክልል ተወካይ የሆኑት አቶ ሪካርዶ ቤቲጋ እና የከተማው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ወ/ሮ ኤሌና ቡቼሚ ይገኙበታል።

የሃሙስ ዕለት ዝግጅቶች በልጆች ላይ የሚደርሰውን በደል እና ውጤታማ በሆነ መልኩ መከላከል የሚቻልባቸው መንገዶችን ለማሳየት ውይይት እንደሚደረግ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ቀድሞ የትምባሆ ፋብሪካ የነበረ አሁን ላይ ግብ የባህልና የሲኒማ ማዕከል የሆነው ተቋም ዝግጅቱን እንደሚያስተናግድ፣ ይህም የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ መንገዶችን ያመቻቻል ተብሏል።

ዓርብ ዕለት በሚኖረው መርሃ ግብር አሁን ባለንበት ወቅት ለወጣቶች አንገብጋቢ ጉዳይ ስለሆነው “የአእምሮ ጤና” ላይ የሚያተኩር ሲሆን፥ ውይይቶቹም ማህበራዊ መገለል እና በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ይዳሰሱበታል ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ታዳጊዎቹ መሃከል ስለሚከሰቱ የማግለል ተግባራትን የሚዳስሰው “ኔላ ሬት” የተሰኘ ቲያትር በሙናሪ ቲያትር ቤት ይታያል ተብሏል።

በዓሉ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ በዕለቱ ተሳታፊዎች የአንትሮፖሎጂ፣ የህክምና እና የፎረንሲክ ሳይንስ ሙዚየም በሆነው ሙሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳይንስን እና ሰብአዊ መብቶችን በማስመልከት ጥናታዊ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህም በተጨማሪ ‘የአርት ቴራፒ’ ወይም ጥበባዊ ህክምናን በተመለከተ አውደ ጥናቶች የሚካሄዱ ሲሆን፥ የሚደረጉት ስፖርታዊ የሰላም ውድድሮች ስፖርትን ለሰላም፣ ለአካታችነት እና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመዋጋት እንደ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።

ቴሬ ዴስ ሆምስ
በ 1952 ዓ.ም. የተመሰረተው ቴሬ ዴስ ሆምስ ፋውንዴሽን ህጻናትን ከጥቃት፣ እንግልት እና ብዝበዛ በመጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፥ ድርጅቱ እያንዳንዱ ልጅ የትምህርት፣ የህክምና አገልግሎት እና ምግብ የማግኘት እድል እንዲኖረው በትጋት የሚሰራ ተቋም ነው።

ቴሬ ዴስ ሆምስ በአሁኑ ጊዜ በ 23 አገሮች ውስጥ በሚገኙ 150 የሚሆኑ ፕሮጀክቶቹ የህፃናት ደህንነት ላይ በማተኮር በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ጭምር ተገልጿል።
 

24 October 2024, 13:41