የሴኡል ሊቀ ጳጳስ ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያገናኛትን ሁሉንም የግንኙነት መስመሮች ማቋረጧ እንደሚያሰጋቸው ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከሴኡል ሊቀ ጳጳስነት በተጨማሪ የፒዮንግያንግ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ብጹእ አቡነ ፒተር በሰሜን እና በደቡብ ኮሪያ መካከል እየጨመረ የመጣውን አለመግባባት በቁጭት ተናግረዋል።
“በደቡብ የሚኖሩ ብዙ ወጣቶች እርቅ ወይም ዳግም መዋሃድ አዋጭ መንገዶች አይደሉም ብለው ማሰብ ጀምረዋል ብዬ አምናለሁ፥ ያሉት ተስፋዎች እየተመናመኑ ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ፒተር ሶን-ታክ ቹንግ በቅርቡ ከቫቲካን ፊደስ የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚወስዱትን መንገዶች እና የባቡር መስመሮችን በመቁረጥ ከባድ እርምጃ የወሰደች ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የሰሜን ኮሪያ ጦር ሁለቱን ሀገራት “ሙሉ በሙሉ የመለየት” እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
ወታደሮቹ እርምጃውን “ጦርነትን ለመግታት እራስን የመከላከል እርምጃ” ሲሉ ገልጸው፣ የደቡብ ድንበርን የማግለል እና በቋሚነት የመዝጋት ዓላማ እንዳለው ገልጿል። ይህ ተምሳሌታዊ ድርጊት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአጎራባች አገሮች መካከል የከፍተኛ ውጥረት መንስኤ ከሆኑት መካከል አንዱ መሆኑን ያመለክታል ተብሏል።
ሊቀ ጳጳስ ቹንግ አሁን ያለውን አስቸጋሪ ጊዜ በመገንዘብ በቀጣይነት ለሰላም መረባረብ እንደሚገባ ካሳሰቡ በኋላ፥ “ሰላማዊ አብሮ የመኖርን እሴትን ማለም እንደሚገባ እና በኮሪያ ማህበረሰብ ውስጥ የተስፋ ብርሃንን ማቆየት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፣ በተለይም አለመግባባት እየጨመረ በመጣበት እና ሙሉ የግንኙነት እገዳዎች ተጠናክረው በቀጠሉበት በአሁኑ ጊዜ ሁኔታዎች በሙሉ ድቅድቅ ጨለማ ሆነዋል” በማለት ተናግረዋል።
የቤተክርስቲያንን ቀጣይ ተልእኮ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት ብጹእነታቸው፥ “ተልዕኳችን ሰላምን ለማስፈን በጸሎትና በትምህርት መቀጠል ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሰላም ምን መደረግ እንዳለበት እና ምን ማድረግ እንደሚቻል ራሷን ትጠይቃለች” ብለዋል።
የጳጳሳዊ የዕርቅ ኮሚሽን ፕሬዘዳንት የሆኑት የቹንቼዮን ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሲሞን ኪም ጁ-ዮንግ የሊቀ ጳጳሱን ስጋት በማስተጋባት፣ በሰብአዊ ጉዳዮች ላይም ሳይቀር የግንኙነት መስመሩ ሙሉ በሙሉ መበላሸቱን የጠቆሙ ሲሆን፥
“ሁለቱም ወገኖች በጥላቻ ስሜት እየተያዩ ነው፥ እያንዳንዱ የመገናኛ መንገድ ተዘግቷል፥ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል ክፍት የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አገልግሎትም ቢሆን ተቋርጧል” ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።
ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዴት መቅረብ እንደሚገባ የተከፋፈሉ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ ብጹእ አቡነ ኪም ግን “ወደ ሰሜን ኮሪያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመላክ ያለውን እድል በተመለከተ ሁሉም የኮሪያ ሕዝብ ይስማማሉ፥ ነገር ግን ሰሜን ኮሪያ የሰብአዊውንም ጨምሮ እያንዳንዱ መንገድ እንዲዘጋ እያደረገች ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
አሁን እየታየ ያለው ሰፊ ዓለም አቀፋዊ አውድ በሰሜን ኮሪያ የቅርብ ጊዜ ድርጊቶች ውስጥ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችል አንዳንድ ዘገባዎች ያሳዩ ሲሆን፥ ታዛቢዎች እንደሚጠቁሙት በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰቱ ግጭቶች አማካይነት የሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ኢኮኖሚዋን በማሳደጉ ምክንያት በውጪ ሃገራት እርዳታ ላይ የነበራትን ጥገኝነት መቀንሱን ይስማሙበታል።
ይህ የኢኮኖሚ ለውጥ የአገዛዙን ከሌላው ዓለም መገለል እየጨመረ መሄዱን እና ከደቡብ ኮሪያ ጋር እንደገና ለመገናኘት እንደማትፈልግ በግልጽ ሊያብራራ ይችላል ተብሏል።