የአካባቢው ማህበረሰብ ለአባ ማርሴሎ ፔሬዝ ቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት በሜክሲኮ ተሰባስበዋል የአካባቢው ማህበረሰብ ለአባ ማርሴሎ ፔሬዝ ቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት በሜክሲኮ ተሰባስበዋል  

ሲኖዶሱ ሰሞኑን በሜክሲኮ ለተገደሉት “የሰላም አርበኛ” ካህን ጸሎት ማድረጉ ተነገረ

የሲኖዶሱ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሜክሲኮ ነባር ተወላጅ ማህበረሰቦች መብት ተሟጋች ለነበሩት ለሟቹ አባ ማርሴሎ ፔሬዝ የህሊና ጸሎት ያደረገ ሲሆን፥ ሲስተር ማሪያ ዴ ሎስ ፓሌንሺያ ጎሜዝ ካህኑ ላይ ግድያ የፈጸሙ ሰዎች “ተገቢው ቅጣት ሳይደረግባቸው ማለፍ የለበትም” በማለት አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በሜክሲኮ ሳን ክሪስቶባል ዴ ላስ ካሳስ ከተማ የኩክሲ-ቲታሊ ደብር ካህን የሆኑት አባ ማርሴሎ ፔሬዝ የተገደሉት መስዋዕተ ቅዳሴ ካሳረጉ በኋላ ነበር ተብሏል።

ከአውሮፓውያኑ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በሜክሲኮ ከ50 በላይ ካህናት የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ዘጠኙ አገሪቷን እየመራት ባለው በአሁኑ አስተዳደር ወቅት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

አንዳንዶቹ የአደንዛዥ ዕጽ ነጋዴዎችን እና ቡድኖችን ጥቃት ተቃውመው በመናገራቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ በተቃናቃኝ የወንጀለኛ ቡድኖች የማያባራ ግጭት መካከል ውስጥ በመገኘታቸው ነው የተገደሉት ተብሏል። ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ለተፈጸሙ ግድያዎች ተጠያቂ የሆነ ወገን የለም፥ አብዛኛዎቹ ግድያዎችም እንዲሁ ተድበስብሰው ቀርተዋል።

የቅዱስ ዮሴፍ እህቶች ማኅበር አባል እና የሲኖዶሱ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ መንበር ተወካይ የሆኑት ሲስተር ማሪያ ደ ሎሬስ ፓሌንሺያ ጎሜዝ የካህኑን ግድያ አስመልክተው ከቫቲካን ዜና ዘጋቢ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የሰላም አርበኛው ካህን
ከተጀመረ 20 ቀናትን ያስቆጠረው የሲኖዶሱ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 21 ቀን ላይ የሲኖዶስ ጉባኤ መክፈቻ መርሃግብር ወቅት ለሟች ካህኑ ጸሎት የተደረገ ሲሆን፥ የሲኖዶሱ ተወካዮች ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን እና ከሜክሲኮ ህዝብ ጋር ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል ሲሉ ሲስተር ማሪያ ተናግረዋል።

ሲስተር ማሪያ ሟቹ ካህን በጣም ድሃ ለሆኑ ህዝቦች ውይይት እና ፍትህ ለማምጣት የሞከሩ የሰላም አርበኛ ነበሩ ያሉ ሲሆን፥ ‘ጦዚል’ ተብለው ለሚጠሩት ነባር የሜክሲኮ ተወላጅ የጎሳ አባላት ለሆኑ ማህበረሰብ መብት ሲሟገቱ እንደነበር እና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሃይማኖታዊ ጥቃት በመቃወም ሲናገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ሲስተር ማሪያ በማከልም የካህኑ ግድያ በማህበረሰቦች ውስጥ መከፋፈል ለመፍጠር የሚሞክሩ ሰዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው ብለውታል።

ቺያፓስ፡ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና በድህነት የሚታወቅ ክልል
የግዳጅ ስደት በሜክሲኮ፣ በተለይም የአባ ማርሴሎ ትውልድ ከተማ በሆነው በቺያፓስ ግዛት ተጠናክሮ መቀጠሉን የተነገረ ሲሆን፥ ቺያፓስ ከደቡብ አሜሪካ፣ እስያ፣ አፍሪካ እና አውሮፓ አገሮች የማያቋርጥ የስደተኞች ፍሰት ያለባት ጓቲማላ ጋር እንደምትዋሰን ጠቁመዋል።

ሲስተር ማሪያ ይሄንን ሲያብራሩ ይህ ፍልሰት ‘ለቱሪዝም፣ ለሁለት ሃገራት ግንኙነት ወይም ለጥናት የሚደረግ ጉዞ ሳይሆን፥ በተለያዩ የህይወት ጫናዎች አማካይነት ተገደው የሚያደርጉት ስደት ነው’ እናም ሰዎች ወደ አስተናጋጅ ሃገራት ሲደርሱ በርካታ ፍላጎቶችን ይዘው ነው በማለት አስረድተዋል።

ቺያፓስ ‘አደንዛዥ እጾችን በሚያዘዋውሩ ነጋዴዎች መካከል በሚደረግ የግዛት ትግል የተነሳ ከፍተኛ ብጥብጥ ከሚገጥማቸው ግዛቶች አንዷ ነች’ ያሉት ሲስተር ማሪያ፥ ‘ኢንሳይት ክራይም’ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሚለው፣ የቺያፓስ ግዛት ወደ አሜሪካ የሚሄዱ መድኃኒቶችን፣ የጦር መሣሪያዎችን እና ስደተኞችን ለማዘዋወር ቁልፍ ቦታ ናት በማለት ገልጸዋል።

ሲስተር ማሪያ እንደተናገሩት ሁከቱ፣ ፉክክሩ፣ ስርቆቱ እና አፈናው ውስጣዊ ፍልሰትን ያስፋፋ እንደሆነ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በማኅበረሰቦች መካከል መለያየትን፣ አለመግባባቶችን እና ለረጅም ጊዜ አብረው በኖሩ ወንድማማች ህዝቦች መካከል አለመተማመን ፈጥሯል” ብለዋል።

በሜክሲኮ ውስጥ የካህናት ግድያ አሁን የጀመር ሳይሆን የዛሬ አስር ዓመት በግፍ የተገደሉት ፓድሬ ኩኮ በመባል የሚታወቁት አባ ሃባ-ኩክ በአካባቢው እንደ ሰማዕት የሚታዩ ሲሆን፥ በሜክሲኮ ውስጥ የተገደሉ ቀሳውስት እና ዲያቆናትም እንደ ሰማዕት ይቆጥራቸዋል።

“ፓድሬ ኩኮ የተገደሉበት ዓመት በግዛቲቷ ያለው ሁከት ከቁጥጥር ውጪ መውጣቱን ያሳየ ነበር” ሲሉ ጓደኞቻቸው ይናገራሉ። “ከዚያ በፊት የነበሩት የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች አካሄዳቸው ምስጢራዊ ነበር። በተወሰነ መልኩ ትንሽም ቢሆን መቆጣጠር ይቻል ነበር፣ አሁን ግን የለየለት ሆኗል” ይላሉ።

አባ ፓድሬ ኩኮ ከተገደሉ አስር ዓመት ቢያልፋቸውም ክስተቱ አሁንም ድረስ አስደንጋጭ እንደሆነ በማህበረሰቡ ይነገራል።

የ39 ዓመቱ ፓድሬ ኩኮ ከሁለት ተማሪዎቻቸው ጋር ወደ አንድ የወጣቶች ዝግጅት እያቀኑ ነበር። ታጣቂዎቹ መኪናቸውን ከበው ተሳፋሪዎቹን እንዲወርዱ አስገደዷቸው። ገዳዮቹ ምንም ቃል ሳይተነፍሱ በመንገድ ዳር ካህኑን ደፏቸው። ከኋላቸውም በርካታ ጊዜ ተኩሰውባቸዋል። በወቅቱም የግድያው ምክንያት ምን እንደሆነ የተባለ ነገር የለም።

ግንዛቤን ማሳደግ                                                                                                                                                         ሜክሲካዊቷ መነኩሴ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በትኩረት እንዲያየው አበክረው በመግለጽ፥ በአባ ማርሴሎ ላይ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እና ፍትህ እንዲሰፍን ካሳሰቡ በኋላ ‘ይህም የሚሆነው በእነዚህ ክልሎች ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር እንዳይረሳ ለማረጋገጥ ነው’ ብለዋል።

የካህኑ ግድያ በዚህ ዓመት በግዛቱ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ውስጥ በጣም የቅርብ ጊዜው ሲሆን፥ በስምንት ወራት ብቻ ወደ 500 የሚጠጉ ግድያዎች እንደተፈጸሙ፥ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ 309 ሰዎች ቁጥር ጭማሪ እንዳሳየ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ሲስተር ማሪያ በመጨረሻም “በሰው ልጅ እና በፍጥረት ላይ የሚፈጸሙ ተከታታይ የሆኑ ጥቃቶች እንዳሉ ለማሳየት ድምጻችንን ከፍ አድርገን ማሰማት እና ዓለም እንዲገነዘብ ብሎም እንዲሰማ ማድረግ አለብን” በማለት አጠቃለዋል።
 

23 October 2024, 13:27