ዩኒሴፍ በጋዛ እየተፈጸመ ያለው የህጻናት ግድያ መቆም አለበት አለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ የእስራኤል ጦር በ 48 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ባደረሰው ጥቃት 50 ህጻናት መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ጥቃቱ ያነጣጠረው በሰሜናዊ ጋዛ በምትገኘው ጃባሊያ ከተማ ላይ እንደሆነ እና ይህች ከተማ ለሳምንታት ያክል በእስራኤል ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ሲደርስባት እንደነበረ አመላክቷል።
እስራኤል ይሄን ጥቃት የምትፈጽመው ሃማስ እንደገና እንዳይደራጅ ለማዳከም እንደሆነ እየገለጸች ትገኛለች።
ይሄን ተከትሎ የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጀምስ ኤልደር በጋዛ የህጻናት ግድያ መቆም አለበት ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ቅዳሜ ዕለት በጋዛ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እየተደረገ እያለ የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን በወሰደው ጥቃት አንድ ጊዜያዊ ክሊኒክ በመምታቱ ሶስት ፍልስጤማውያን ህጻናት መጎዳታቸው ተነግሯል።
ይህ ድርጊት የተፈጸመው በጋዛ ከተማ የጤና ሰራተኞች ከ10 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ድንገተኛ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እያስጀመሩ ባለበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
ዘመቻው ከዚህን ቀደም በማዕከላዊ እና በደቡባዊ ጋዛ እየተካሄደ የነበረ ሲሆን፥ ነገር ግን ተለዋዋጭ በሆነው ወታደራዊ ሁኔታ ምክንያት በሰሜን በኩል ለሌላ ጊዜ ተላልፎ እንደነበር ተነግሯል።
በሌላ ዜና የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር አርብ ዕለት በእስራኤላዊያን ኮማንዶዎች ታፍነው በተወሰዱት የሊባኖስ ባህር ሃይል ካፒቴን ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዋል።
ሊባኖስ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ አቤቱታ ልታቀርብ እንደሆነም ተገልጿል።