ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከበረው የዓለም የህፃናት ቀን ላይ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከበረው የዓለም የህፃናት ቀን ላይ  

በዘንድሮው የዓለም ህፃናት ቀን “እያንዳንዱ ልጅ ሙሉ መብቱ ሊጠበቅ ይገባል” የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ተከብሯል

የዓለም የህጻናት ቀንን ምክንያት በማድረግ የተባበሩት መንግስታት ከእያንዳንዱ የህይወት ዘርፍ የተውጣጡ ሰዎችን በመጋበዝ የልጆችን ድምጽ እንዲያዳምጡ እና የተሻለ ዓለም እንዲፈጥሩላቸው ጥረት እያደረገ መሆኑ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በየዓመቱ ህዳር 11 በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም ህፃናት ቀን የሚከበር ሲሆን፥ ይህ ዓለም አቀፋዊ ክስተት ስለ ህፃናት መብት ግንዛቤን ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ አንድነትን ለማጎልበት እና ደህንነታቸውን ለማሻሻል ታስቦ የሚከበር ነው።

የዘንድሮ የዓለም ህፃናት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ እንደሚከበር የተነገረ ሲሆን፥ ቀኑ "ህፃናት የሚሉት አላቸው እና እናድምጣቸው!" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተከበረው።

እ.አ.አ. በ1954 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተው የዓለም ህፃናት ቀን የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ሁለቱንም የህጻናት መብቶች ኮንቬንሽን እና አዋጅ ያፀደቀበትን ቀንን በማስታወስ ይከብራል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ህጻናት በሰላም እና በስምምነት የሚኖሩባቸው ማህበረሰቦችን፣ ህብረተሰብን እና ሀገራትን በመፍጠር ረገድ በበዓሉ ላይ ህጻናትን ጨምሮ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎችን ይጋብዛል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጥልቅ በተከፋፈለ፣ ግርግር በበዛበት እና በርካታ ጥቃቶች በሚፈጸሙባት ዓለም ውስጥ ያሉ ህፃናት የሚያጋጥሟቸውን ከባድ ፈተናዎችን በማስታወስ፥ “በዚህ ቀን ከሰብዓዊ ቤተሰቦቻችን ውስጥ የታናናሽ አባላትን ቀን እናከብራለን” በማለት ስለ ልጆች መብት ታስቦ የሚውልበት ቀን መሆኑን ጠቁመዋል።

የዓለም የህፃናት ቀን ለእያንዳንዱ ሰው የልጆችን መብቶች ለማክበር እና ለእድገታቸው ምቹ ቦታዎችን ለመፍጠር እድል ይሰጣልም ተብሏል።

ዓለም አቀፍ የድርጊት ቀን
ይህ በዓል ምሳሌያዊ ብቻ ሳይሆን የተግባርና የተጠያቂነት ጥሪ የሚተላለፍበት ቀን ጭምርም እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ዘንድሮ የተከበረውን ይህንን የህፃናት ቀን ለህፃናት እና በህፃናት “ዓለም አቀፍ የድርጊት ቀን” በማለት እንዳወጀ፥ ከዚህም ባለፈ የህጻናት መብቶች ስምምነት ማፅደቁን በማመልከት፣ ይህም ስምምነት በህፃናት ልጆች ላይ ሊተገበሩ የሚገቡ የስነምግባር መርሆዎችን እና የህግ ደረጃዎችን የያዘ እንደሆነ ገልጿል።

“የህጻናት መብቶች ሰብአዊ መብቶች ናቸው” ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፅንዖት ሰጥቶ በመግለፅ፥ እነዚህ መብቶች ዓለም አቀፋዊ፣ ለድርድር የማይቀርቡ እና ለማንኛውም ማህበረሰብ እድገት መሰረታዊ ናቸው በማለት አሳስቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው የህጻናት መብት በማይከበርበት እና በሚናቅበት ዓለም ውስጥ፣ ህጻናት ፍላጎቶቻቸውን እና ሃሳቦቻቸውን በራሳቸው የመግለጽ መብት እንዲረዱ እና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች ዛሬ በምናከናውናቸው ድርጊቶቻችን ውስጥ ለማካተት ህፃናትን ማዳመጥ እንደሚገባ አፅንዖት በመስጠት ገልጿል።

የህፃናት መብቶች
በዓለም ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በበሽታዎች መጠቃታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ደግሞ የጥቃት፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ የዓመፅ እና የጦርነት ሰለባ እንደሆኑ ይነገራል። ከዚህም በላይ በርካታ ልጃገረዶች ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት ዕድል እንደሌላቸውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

ዩኒሴፍ እና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች በአደገኛ ወይም በአሳሳቢ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት የትምህርት፣ የምክር አገልግሎት እና እንክብካቤ የሚሰጡ ፕሮግራሞችን በመደገፍ እና መብቶቻቸው እንዳይጣሱ አጥብቀው በመስራት የህጻናትን መብቶች ለማስከበር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
 

21 November 2024, 14:49