በዓለማችን ከ3 ቢሊዮን በላይ ሰዎች የጤና አጠባበቅ ችግር እንዳለባቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዓለም ዙሪያ 3.5 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አስተማማኝ ክትትል በማይደረግላቸው የንጽህና አጠባበቅ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ሌሎች 2 ቢሊዮን ሰዎች መሠረታዊ የንፅህና አግልግሎት እንደሌላቸው የገለጸው ድርጅቱ፥ ለችግሩ ከተጋለጡት መካከል ብዙዎቹ ስደተኞች እና ድሃ ማኅበረሰቦች እንደሆኑ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በየጊዜው በሚለዋወጥ እና በመዘመን ላይ በሚገኝ ዓለም ውስጥ እነዚህን መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶችን በየዕለቱ የሚነፈጉ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ለማሳሰብ በየዓመቱ ህዳር 19 “የዓለም የመፀዳጃ ቀን” ብሎ በመደንገግ ትኩረትን እንደሚስብ ታውቋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ማለት ደህንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ ማለት ነው
በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት የውሃ እና የንጽህና አጠባበቅ ክፍል ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ብሩስ ጎርደን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳብራሩት፥ ብዙ ወጣት ልጃገረዶች እና ሴቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው በቂ ብርሃን በሌሉባቸው አደገኛ አካባቢዎች የሚገኙ መጸዳጃ ቤቶችን ለመጠቀም እስከ ምሽት ድረስ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ከጤና ጥያቄ ጋር አብሮ የሚሄድ ሌላው ጉዳይ የሰው ልጅ መሠረታዊ ክብር እንደሆነ የገለጹት አቶ ብሩስ ጎርደን፥ “ደህንነቱ የተጠበቀ እና ትክክለኛ መገልገያዎችን ማግኘት የሁሉ ሰው መብት እና መሠረታዊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል
ትክክለኛ መገልገያዎች ወደ ጤናማ ሕይወት ይመራሉ
ትክክለኛ የንጽሕና መገልገያዎች ተደራሽነት ከማኅበረሰቡ ጤና ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን አቶ ብሩስ ጎርደን አስረድተዋል።
የውሃ ፍላጎት ከዓለማችን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር ሲወዳደር በልጦ መገኘቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሪፖርቱ አስታውቆ፥ ከዓለም ሕዝብ መካከል ቢያንስ ግማሹ በዓመት ለአንድ ወር ያህል ከባድ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥመው በማስረዳት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 1,000 ሕጻናት ንጹሕ ባልሆነ ውሃ እና በንጽህና አጠባበቅ እጦት በሚመጡ በሽታዎች በየቀኑ እንደሚሞቱ ገልጿል።
“ለውሃ ወለድ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤው ደካማ የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓት ነው” ያለው ሪፖርቱ፥ በዚህ ላይ አንድ ነገር ማድረግ ከተቻለ ሌሎችን በርካታ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት ይቻላል” ሲል አስረድቷል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደ የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ ካሉ ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በዓለም ዙሪያ ደህንነቱ የተጠበቀ ትክክለኛ መገልገያዎችን ለማቅረብ፣ ግንዛቤን ለማሳደግ እና ትብብርን ለማጎልበት ዝግጅት እንደሚያደርግ ታውቋል።
“የጤና አጠባበቅ እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ለሁሉ ማቅረብ” የሚለው መርሃ ግብር መንግሥታትን በማስተባበር የሀገር መሪዎች ደኅንነታቸውን የጠበቁ ተቋማት የመመሥረት ውጥኖችን እንዲያበረታቱ የሚያድርግ እና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅትም በበኩሉ ስደተኞቹ የትም አገር ቢሆኑ ንፁህ ውሃ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አታውቋል።