የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

ጋዛ ውስጥ በፍልስጤማውያን ላይ የሚደርስ የሞት አደጋ መቀጠሉ ተገለጸ

በሰሜን ጋዛ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ የመጨረሻዎቹ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ታካሚዎችን እንዲያስወጣ የእስራኤል ጦር ማስገደዱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሆስፒታሉ ሠራተኞች እንደሚሉት፣ የእስራኤል ጦር በክሊኒኩ አካባቢ ባነጣጠረው ጥቃት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

የሆስፒታሉ የነርሲንግ ክፍል ሃላፊው እንደገለጹት፥ የእስራኤል ወታደሮች አስተዳደሩ ሕሙማንን እና ሠራተኞቹን ከተቋሙ እንዲያስወጣ 15 ደቂቃ ብቻ መስጠቱን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃማስ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የጤና ተቋሙ፣ የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በጋዛ ሰርጥ ሃማስ ላይ በፈጸመው ከፍተኛ ጥቃት 37 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

ከ45,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል
ጋዛ ውስጥ ካለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጀምሮ የተረጋገጠው የሟቾች ቁጥር 45,436 መድረሱን የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ባሉት 14 ወራት ውስጥ 108,038 ፍልስጤማውያን ቆስለዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል የየመን ሁቲዎች በቴላቪቭ በሚገኘው የእስራኤል ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ “ሃይፐርሶኒክ ባሊስቲክ ሚሳኤል” ማስወንጨፉን ተናግሯል። ይሁን እንጂ እስራኤል ሚሳኤሉን እንዳከሸፈችው ተናግራለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስራኤል የባሕር ጠረፍ ከተማ ሄርዝሊያ ውስጥ በ80ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንዲት ሴት በቢላዋ በደረሰባት ጥቃት ሕይወቷ አልፏል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ዓርብ ጠዋት ሲሆን፥ ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለው ተጠርጣሪ በቦታው በነበሩ የጥበቃ አባላት በጥይት ተመትቶ መያዙ ታውቋል።

 

28 December 2024, 13:42