ለጋዛ የሚሰጠው የሰብአዊ እርዳታ ላለፉት ሁለት ወራት 'በአብዛኛው ታግዶ’ እንደነበር ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ላለፉት 66 ቀናት ለጋዛ የሚደረገው ሰብአዊ እርዳታ በአብዛኛው መታገዱን በመግለጽ፥ በዚህም ምክንያት ወደ 75,000 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ምግብ፣ ውሃ፣ መብራት ወይም ማንኛውንም ዓይነት የጤና አገልግሎት አያገኙም ተብሎ ይታሰባል ብሏል።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ 26,000 የሚገመቱ ፍልስጤማውያን ባለፈው ዓመት በደረሰባቸው ጉዳት እየተሰቃዩ ሲሆን፥ በተለይ አካል ጉዳተኞች በመልሶ ማቋቋም አገልግሎት እጦት እና በቂ የአጋዥ መሣሪያዎች እጥረት ምክንያት በከባድ የአዕምሮ ጭንቀት እየተሰቃዩ መሆኑ ተገልጿል።
ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በጋዛ ውስጥ ይከናወኑ ከነበሩ 273 የዓለም ጤና ድርጅት ተልእኮዎች ውስጥ 58 በመቶው ውድቅ ተደርገዋል፣ ተሰርዘዋል ወይም ተሰናክለዋል። ይህ አስቸኳይ ነገር ግን እጅግ በጣም ከባድ የሆነውን ከክልሉ ውጭ ልዩ የሕክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎችን የማስወጣት ሥራንም እንደሚያካትት ተገልጿል።
ቀደም ሲል በጋዛ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊነት እና የመልሶ ግንባታ አስተባባሪ ሲግሪድ ካግ እንደተናገሩት ሲቪሎች “ፍፁም አስከፊ ሁኔታ” እያጋጠማቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) በበኩሉ እንደገለጸው በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ በተባበሩት መንግስታት የሚደገፉ አራት ዳቦ ቤቶች የሚገኙት ሁሉም በጋዛ ከተማ ውስጥ ብቻ እንደሆነ አመላክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋዛ እና በዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሰብአዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ቢያንስ 6.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ግምቱን አስቀምጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዛ ሲቪል መከላከያን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው በሰሜን ጋዛ በምትገኘው ቤይት ላህያ ከተማ ላይ እስራኤል ከፈጸመችው ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ በኋላ በትንሹ 22 ሰዎች መገደላቸውን እና የከማል አድዋን ሆስፒታል ሟቾችን መቀበሉን የገለጸ ቢሆንም፥ የእስራኤል መከላከያ ቢሮ ስለ ጥቃቱ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።