አንዲት ሴት በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው አል ያርሙክ የፍልስጤማዊያን የስደተኞች ካምፕ አከባቢ ቆማ  አንዲት ሴት በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው አል ያርሙክ የፍልስጤማዊያን የስደተኞች ካምፕ አከባቢ ቆማ  

በሶሪያ ሁሉን አቀፍ የሆነ ሥርዓት እንደሚገነባ ተስፋ አለ ተባለ

በሶርያ የጄሲዩት ስደተኞች አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አባ ቪንሰንት ዴ ቢኩድሪ በሀገሪቱ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፥ በመጀመሪያ አከባቢ በሆምስ ከተማ አሁን ደግሞ በደማስቆ በማገልገል ላይ እንደሚገኙ እና ህዝቡ አሁን እየደረሰበት ላለው ግርግር ለመናገር ትክክለኛ ምስክር ናቸው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሶሪያዋ ዋና ከተማ ደማስቆ የቀድሞው አገዛዝ ፈርሶ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት በሽር አል አሳድ ወደ ሞስኮ ከሸሹ በኋላ፣ ሃገሪቱን እያስተዳደሩ የሚገኙት ሃይላት ስለ አላማቸው እና ስለሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ በማንሳት ህዝቡን በማረጋጋት ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ በህዝቡ ዘንድ ሲታይ የነበሩት የደስታ ትዕይንቶች ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ ጀምረዋል።

ምንም እንኳን ቡድኑ ከአክራሪ እስላማዊነት ጋር የጠበቀ ታሪካዊ ግንኙነት ቢኖረውም የሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) አማፂያን መሪ የሆኑት አቡ መሀመድ አል ጆላኒ ለሁሉም ማህበረሰብ እኩል መብት የሚሰጥበት “ሁሉን አቀፍ” የሆነች ሶሪያን መገንባት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

አባ ቪንሴንት በሆምስ ከተማ በርካታ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ አሁን ላይ በዋና ከተማዋ ደማስቆ የሚገኙ ሲሆን፥ በሶሪያ የኢየሱሳዊያን የስደተኞች አገልግሎት ቅርንጫፍን እየመሩ ይገኛሉ።

ካህኑ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ሶሪያ አሁን ስላለችበት ሁኔታ በትልቅ ተስፋ እና እርግጠኛ ባልሆነ ስሜት ውስጥ ሆነው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በሆምስ ከተማ ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው የነበሩት አባ ቪንሴንት ያኔ የነበረው ሁኔታ ከአሁኑ ፍጹም ይለይ እንደነበር በማስታወስ፥ በሶሪያ ውስጥ ከተከሰቱት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች አንፃር እና አሁን በደማስቆ ስላለው ሁኔታ መካከል ያለውን ልዩነት ሲገልጹ፥ ብዙ ጉልህ የሆኑ ልዩነቶች እንዳሉ፥ ሆኖም ግን በእርግጥ ብዙ ተመሳሳይነቶችም እንዳሉ ጠቁመዋል። ፖለቲካዊ መልኩ እና የነበሩት ስጋቶችም ፍጹም የተለየ እንደነበር ያስታወሱት ካህኑ፥ ያለው እውነታ ግን ሀገሪቱ እንደፈረሰች፣ ኢኮኖሚው እንደወደመ፥ ብሎም በርካታ ሰዎችም እንደተፈናቀሉ በመጥቀስ ዛሬ ላይ በጣም እርግጠኛ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ጠቁመው “ዛሬ ሶሪያን የሚገልጸው ይሄ ነው፥ እርግጠኝነት ባለመኖሩ በየቀኑ እቅዶችህን ለመቀየር ትገደዳለህ፥ ነገ ምን እንደሚመጣ አታውቅም፥ በአሥር ቀናት ውስጥ ሁሉም ነገር ተለውጧል፥ ይህ እርግጠኛ ያለመሆን ሁኔታ ተስፋ ሊፈጥር ይችላል፣ ነገሮች እየተለወጡ ስለሆነ የተወሰነ ደስታን ሊያመጣም ይችላል፥ በመሆኑም እኛም ብዙ ነገሮች እንዲለወጡ እንፈልጋለን፥ በተቃራኒው ግን ፍርሃትንም ይፈጥራል” ብለዋል።

በየቀኑ የሚያገኟቸው ሶሪያውያን ከቅርብ ቀናት ወዲህ ሃሳባቸውን በነፃነት እየገለጹ እንደሆነ የተጠየቁት ካህኑ፥ “አዎ፣ ሰዎች በነፃነት የሚናገሩባቸው ርዕሶች አሉ፥ አሁን ስለ ሴድ-ናያ ማለትም የአገዛዙ የፖለቲካ እስረኞች ታስረውበት ስለነበረው እስር ቤት ያለ ምንም ችግር ማውራት ይችላሉ፣ ስለ ወታደራዊ ግዳጅም ማውራት ይችላሉ፣ ነገር ግን አሁንም ውስብስብ የሆኑ ሌሎች ነገሮች አሉ” ካሉ በኋላ እንዴት በልዩነት ውስጥ አንድ ህዝብ መመስረት እንደሚቻል ማውራት አሁንም ከባድ እንደሆነ በመግለጽ፥ ትንሽ ከበፊቱ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የሃይማኖት ልዩነቶችን ለመፍታት አሁንም የተወሳሰበ ነው ብለዋል።

ስለሃይማኖት ልዩነቶች ሲነሳ በሶሪያ ውስጥ ክርስቲያኖችን ጨምሮ በርካታ ማህበረሰቦች እንዳሉ እና ብዙ ክርስቲያኖች ሃገሪቷን ለቀው እንደወጡ ይታወቃል፥ በቅርብ ቀናት ውስጥ ብዙ ሶሪያውያን እንዳደረጉት አንዳንዶች ለመመለስ ሊሞክሩ ይችላሉ። ነገር ግን ክርስቲያኖች ለምሳሌ መጪውን የገናን በዓል በሰላም ለማክበር እንደሚችሉ ማረጋገጫ ወይም ቢያንስ ተስፋ እንዳላቸው የተጠየቁት አባ ቪንሰንት፥ በቅርብ ቀናት ውስጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስለጉዳዩ መነጋገር ከቻሉ በሰላም ማክበር እንደሚቻል ገልጸው፥ አዲሶቹ ባለ ሥልጣናት እንደሚናገሩት ከክርስቲያኖች ጋር በመሆን ሶሪያን መመስረት እንደሚፈልጉ ጠቁመው፥ አሁን ለአሥር ቀናት በቆዩበት አሌፖ ከተማ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚደረጉ የተለያዩ የገና ጌጣጌጦችን መፍቀዳቸውን፣ ይህም ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ እና የገና በዓልን በሰላም ለማክበር የሚቻልበት ምልክቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ዛሬን ከመጨነቅ ይልቅ ተስፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክንያቶች ካሉ ተጠይቀው፥ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፥ ነገር ግን ክርስቲያን ተስፋ እንደማይቆርጥ በመጠቆም፥ ሁሉንም ነገር በጊዜው ወረቀት ላይ ብናሰፍረው አሁንም የተጠናቀቀ ስምምነት ስላልሆነ የተስፋ ምልክት ሊሆን አይችልም ብለዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ሆምስ ከተማ በነበሩበት ወቅት ወጣቶች ካህኑን ሊጠይቋቸው በሚመጡበት ጊዜ በሃገራቸው እንዲቆዩ የሚያበረታታቸው ነገር እንደሌለ ይነግሯቸው ነበር፥ ካህኑ እንደሚናገሩት ዛሬም ቢሆን ወጣቶቹ ለቀው እንዲሄዱ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲቆዩም እንደማይመክሯቸው ገልጸው፥ “እኔ ማን ስለሆንኩ ነው የምወስንላቸው?” በማለት ጠይቀዋል።

በቅርብ ሳምንታት ያየናቸው ለውጦች ለወጣቶቹ በሃገራቸው የመቆየት ምክንያት ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ ያሉት ካህኑ፥ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በእርግጠኝነት የሚወስኑበት ወቅት አይደለም ብለዋል።

ወደ ደማስቆ የተመለሱ ስደተኞች እንዳሉ የጠቆሙት አባ ቪንሰንት፥ ከተመላሾቹም ጋር አብረው እየሰሩ መሆኑን በመግለጽ፥ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ብዙ ርቀው የተጓዙ እንዳልሆኑ እና በስደተኛ ካምፖች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ፣ ብሎም በፖለቲካዊ ምክንያቶች መመለስ የማይችሉ ከሊባኖስ እና ከቱርክ የመጡ ናቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ከተነሱ ሀገሪቱ እንደገና መገንባት እንደምትጀምር ተስፋ አለኝ ያሉት ካህኑ፥ ሆኖም ግን አሁን ላይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማዕቀቡን ከማንሳቱ እና በሶሪያ ኤምባሲዎችን ከመክፈቱ በፊት ስለ ስደተኞች መመለስ እንደማያሳስበው አዝማሚያ በማሳየቱ አሳዝኖኛል ብለዋል።

ካህኑ በማከልም አገሪቱ ሰላም ናት ብለው ካመኑ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተው ግንኙነት መፍጠር፣ ሁኔታውን ማወቅ፣ ማዕቀቡን ማንሳት እና ከዚያ በኋላ ስደተኞች መመለስ ይችላሉ ወይም አለባቸው ማለት ተገቢ ነው ብለዋል። ‘ይህ የመጀመሪያው ነገር ነው’ ያሉት አባ ቪንሰንት፥ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ማዕቀቡን ማንሳት በእርግጥ አስፈላጊ እርምጃ ነው ብለዋል።

በሰብአዊ እርዳታ ብቻ ሳይሆን በንግድ ኢንቨስትመንቶች፣ የሶሪያን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎችም እንደሚያስፈልጉም ጭምር አንስተዋል። ከዚህ በመነሳት ኤምባሲዎችን እንደገና ከመክፈት እና ማዕቀቡን ከማንሳታቸው በፊት ሀገራት ግድግዳዎችን ሲገነቡ ማየት በጣም አስደንጋጭ ነገር ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ክርስቲያኖች የከፈሉት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለ የገለጹት ካህኑ፥ ይህ መስዋዕትነት “እኛ ቤታችን እዚህ ነው፤ እኛም የምድር ጨው ነን” የሚሉ ሰዎች መስዋዕትነት እንደሆነ፣ የከፈሉትም ዋጋ በከንቱ እንዳልነበረ ገልጸዋል።

በቅርብ ወራት ውስጥ ወደ ደማስቆ እንደተመለሰ ሰው በግል ምን እንደሚሰማቸው የተጠየቁት አባ ቪንሰንት በመጨረሻም፥ የእሳቸው ስሜት የነገውን ፍርሃትና ጭንቀት ተቀብሎ ከህዝቡ ጋር ለመኖር መሞከር እንደሆነ በማስታወስ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም ኃይለኛ እየሆነ በመጣው የእስራኤል የቦምብ ጥቃቶች ጨምሮ፣ አንዳንዴ በፍርሃት እንደሚረበሹ ጠቁመው፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ምንም እንኳን የኋላ ታሪካቸው ኢስላማዊ አካሄድ እንደነበራቸው ቢያሳይም፣ አሁን ላይ ‘ሁሉን ያቀፈች ሶርያ ውስጥ መኖር እንፈልጋለን’ እያሉ የሚገኙትን አዲሶቹን መሪዎች በቁም ነገር በመቀበል ችግሮችን በጋራ ልንፈታ እንደምንችል ማመን እና መሞከር ያለብን ይመስለኛል ብለዋል።
 

17 December 2024, 13:50