ስደተኞች ከብሔራዊ የስደተኞች ኢንስቲትዩት ቢሮ መግቢያ በር ላይ ተሰልፈው ስደተኞች ከብሔራዊ የስደተኞች ኢንስቲትዩት ቢሮ መግቢያ በር ላይ ተሰልፈው 

ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር አዋለች

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ካዋለች በኋላ ሜክሲኮ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚደረገውን ህገ-ወጥ የስደት ሙከራ ለመግታት ሥራ እንደጀመረች አስታወቀች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሜክሲኮ ከመካከለኛው እና ከደቡብ አሜሪካ የሚደረጉትን የስደት ጉዞዎች ለመግታት ጥረት እያደረገች ያለው ‘ፍሰቱት ማስቆም’ በሚለው አዲሱ ፖሊሲዋ አማካኝነት እንደሆነ ገልፃለች።

የሜክሲኮ ባለስልጣናት ከመስከረም 21 እስከ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ጋር በመተባበር ድንበር ላይ የደረሱ 475,000 ህገ-ወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፥ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ሲታይ ይህ አሃዝ ወደ 900,000 እንደሚደርስ ተገልጿል።

የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁዋን ራሞን ዴ ላ ፉዌንቴ ይህ ፖሊሲ በተሳካ ሁኔታ እየተተገበረ ቢሆንም የበለጠ ሊሻሻል እንደሚገባው ገልጸው፥ በህዳር ወር አጋማሽ ላይ የታሰሩት ሰዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ81 በመቶ ቀንሷል ብለዋል።

የዚህን ምክንያት ሲገልጹ በዩናይትድ ስቴትስ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ ከፍተኛ ጥበቃ መደረግ ስለተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ቀደም ባሉት ጊዜያት የጥበቃ ክፍተት እንደነበር፣ አሁን ላይ ግን የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ በመሆኑ ከፍተኛ የስደተኞች ክምችት በሜክሲኮ ድንበር ውስጥ እንዲከሰት አድርጓል ብለዋል።

ቀደም ሲል የሚያዙት ሰዎች ቁጥር ከተሻገሩት ሰዎች ቁጥር ያንስ እንደነበር፣ አሁን ላይ ግን አብዛኞቹ ሳይሻገሩ እዚያው ሜክሲኮ ድንበር ላይ እንደሚቀሩ ተገልጿል።

በሜክሲኮ ኢኮኖሚያዊ ማበረታቻዎች በቂ ባለመሆናቸው ህዝቡ ቋሚ የመኖሪያ ቦታ ስለማያገኝ እና ከፍተኛ ሥራ እጦት ስላለ አብዛኛውን ነዋሪ ተረጋግቶ እንዳይኖር እና ለስደት እንዲገፋፋ በር ከፍቷል ተብሏል።

ሆኖም ግን ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሜክሲኮ የህገ-ወጥ አደንዛዥ እጾች እና የስደተኞች ፍሰትን እስካልቀነሰች ድረስ ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ሃያ አምስት በመቶ ቀረጥ እንደሚጥል በመግለጹ ምክንያት ለአዲሱ የሜክሲኮ አስተዳደር ይህ ሁኔታ ዋነኛ የፖለቲካ ጉዳይ መሆኑ እየታየ መጥቷል።

ፕሬዝዳንት ሺንባም ህዳር ወር ላይ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ይህንን ጉዳይ ለመፍታት ቃል የገቡ ሲሆን፥ ስደተኞች ብዙውን ጊዜ ወደ ድንበሩ አከባቢ እየደረሱ ቢሆንም ነገር ግን በሁለቱም ሃገራት በኩል በሚደረገው የተጠናከረ ደህንነት ምክንያት ድንበሩን ሊሻገሩ እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ይህ ግን ስደቱ ለምን ቀጠለ የሚለውን መሰረታዊ እና አጠቃላይ ችግር አይፈታውም ወይም መፍትሄ አይሰጠውም። ችግሩ የሚከሰተው በከፋ ድህነት፣ በአገር ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎች እጦት እና ህገ-ወጥ ቡድኖች ወጣቶችን ወደ ራሳቸው ለማጥመድ የሚያደርጉትን ተግባራት በመሸሽ እና በመሳሰሉት ነገሮች ለስደት እንደሚዳርጉ ተገልጿል።

ብዙ ጊዜ ስደተኞችን ጠልፈው የቤዛ ገንዘብ የሚጠይቁ የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ከፍተኛ እንግልት የሚደርስባቸው ቢሆንም በሺዎች የሚቆጠሩ ምንም ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች አደገኛውን ጉዞ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፥ በዚህም ገንዘቡን መክፈል የማይችሉ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይወድቃሉ።

አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የሜክሲኮን ሰፊ ግዛት ለማቋረጥ ሲሞክሩ ከ20,000 የሚበልጡ ስደተኞች በቋሚነት ጠፍተው የሚቀሩ ሲሆን፥ በርካታ አስከሬኖች ብዙውን ጊዜ በበረሃማ ድብቅ የመቃብር ስፍራዎች ውስጥ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ።
 

30 December 2024, 12:39