በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተፈጠረው ግጭት የእስራኤልን ጥቃት ሸሽተው ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱት ፍልስጤማውያን በራፋህ አከባቢ ባለው ከፍተኛ ዝናብ እና ቅዝቃዜ ምክንያት  ድንኳኖቻቸው አጠገብ እሳት አቀጣጥለው ሲሞቁ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተፈጠረው ግጭት የእስራኤልን ጥቃት ሸሽተው ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱት ፍልስጤማውያን በራፋህ አከባቢ ባለው ከፍተኛ ዝናብ እና ቅዝቃዜ ምክንያት ድንኳኖቻቸው አጠገብ እሳት አቀጣጥለው ሲሞቁ 

በጋዛ አዲስ የሚወለዱ ሕፃናት በብርድ ምክንያት ለሞት እየተጋለጡ እንደሆነ ተነገረ

በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ባለው ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በጋዛ የሚገኙ የጤና ባለስልጣናት እንዳረጋገጡት ‘ሃይፖተርሚያ’ ተብሎ በሚታወቀው የብርድ በሽታ በትንሹ አራት ጨቅላ ህጻናት መሞታቸውን ተዘግቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ የሆነው ዩኒሴፍ ሰሞኑን እንደገለጸው እስራኤል በጋዛ ላይ ከምትወስዳቸው ጥቃቶች በተጨማሪ በአከባቢው የሚገኙ ህጻናት በአሁኑ ወቅት በብርድ እና በበቂ መጠለያ እጦት ምክንያት እየሞቱ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የዩኒሴፍ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ኤድዋርድ ቤይግደር እንደተናገሩት “እነዚህ በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ የነበሩ ሞቶች በጋዛ የሚገኙ ቤተሰቦች እና ህፃናት የሚኖሩበትን ተስፋ አስቆራጭ እና የከፋ ሁኔታ ያሳያሉ” ብለዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ የእስራኤል የጤና ባለስልጣናት ከሃማስ የተለቀቁ የእስራኤል ዜጎችን ጤንነት አስመልክቶ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚያቀርቡትን ሪፖርት ማጠናቀቃቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት እስረኞቹ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ታግተው በነበሩበት ወቅት ከ 10-17 በመቶ የሰውነት ክብደታቸው እንደቀነሰ፣ ድብደባ እና ማግለልን ጨምሮ በርካታ ችግሮች እንዳጋጠሟቸው፣ ብሎም ህጻናት ላይ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እና ሴቶችም ለወሲብ ጥቃት እንደተዳረጉ አመላክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ታጋቾቹ ትክክለኛ የሕክምና አገልግሎት እንዳልነበራቸው፣ በዚህም ምክንያት አንዳንድ አዛውንቶች ለረጅም ጊዜያት በእገታ ሥር በነበሩበት ወቅት ‘ቲሮምቦሲስ’ ለተባለ የልብ በሽታ መጋለጣቸው ተገልጿል።

በሆስፒታል ውስጥ የተከናወነ ወታደራዊ ዘመቻ
በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው ካማል አድዋን ሆስፒታል ላይ የወሰደውን ወታደራዊ ዘመቻ ማጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን፥ ወታደራዊ ኃይሉ በፈጸመው ወረራ ምክንያት ሆስፒታሉ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል።

በወታደራዊ ዘመቻው የእስራኤል ጦር የሃማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ የተሰኘው አክራሪ ቡድን አባላት ናቸው ያላቸውን 240 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ዘገባዎች የጠቆሙ ሲሆን፥ ከነዚህም በተጨማሪ ጦሩ የሆስፒታሉን ዳይሬክተር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጋዛ ውስጥ ህዝቡ የጤና ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ እንደነበር ይታወቃል።
 

30 December 2024, 12:28