ሱዳን የተረሳች አገር ብትሆንም ተስፋ የምታደርግ መሆኗ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሱዳን የቀጠለውን ጦርነት እና ቀውስ በማስመልከት ለዕርዳታ ሠራተኞች ብዙውን ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ነገር ግን ማንም መልስ የማይሰጠው ጉዳይ ሆኗል። “የሱዳን ጦርነት አንገብጋቢ እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ እያለ ነገር ግን ማንም ሰው ማስረዳት የማይችለው የሆነበት ለምንድነው? አንዳንድ ጦርነቶች ከሌሎች ጦርነቶች ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ለምንድነው? ጦርነቶች እየተካሄዱ ባሉበት ወቅት ዕይታችን ወደ ሌላ አቅጣጫ የምናዞረው ለምንድነው?” የሚሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።
ከጦርነት እና ከጦር መሣሪያ ንግድ የሚመነጩ የተለያዩ ከሥነ-ምግባር አኳያ የተናቁ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እናዳሉ ብንገነዘብም በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ እና ስቃይ በዝምታ መመልከት የለብንም።
“ሁሉም ዓይኖች በሱዳን ላይ ናቸው”
የሁሉም ሰው ሕይወት እኩል ከሆነ የሱዳን ሕዝብ ሕይወት ከሞት ለመጠበቅ ለምን ብዙ አልተሰራም? ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ሀገር ከ61,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና 12 ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ መፈናቀላቸውን ስናነብ ይህ ዜና ለምን ግንባር ቀደም ዜና ሆኖ ያልቀረበበትን ለመረዳት ያስቸግራል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ሃያ ስድስት ሚሊዮን ሱዳናውያን ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል ሲል ይህ ቁጥር በሱዳን ውስጥ እጅግ በጣም የከፋ የረሃብ ቀውስ እንዳለ ይናገራል።
ጦርነቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተስፋፍቶ ቢገኝም ነገር ግን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) እና በሱዳን ጦር ሃይሎች መካከል 20 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት በምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ግዛት ውስጥ የሚፈጸመው የአየር ድብደባ መጨመሩ በሲቪል ማኅበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ከፍተኛ ስቃይ አሳሳቢ መሆኑን ታዛቢዎች ገልጸዋል። በሱዳን ሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረስ ላይ የሚገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ሰጭ ድርጅት “ካፎድ” CAFOD ዋና ኃላፊ የሆኑት ሚስተር ቴሊ ሳዲያ፥ ሁኔታ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ እና ሲቪሎች የዚህ የማያባራ ጦርነት ሰለባዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚስተር ቴሊ ሳዲያ በሱዳን ከሚገኘው የካቶሊክ በጎ አድራጎት የባሕር ማዶ ዕርዳታ ስጭ ኤጀንሲ “ካሪታስ” ቅርንጫፍ ጋር በመሆን የዕርዳታ ድርጅታቸው የሱዳናውያን ጩኸት ይበልጥ እንዲሰማ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል። ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሚስተር ሳዲያ፥ “ሱዳን ውስጥ ሳያቋርጥ የቀጠለው ጦርነት ሰፊ መፈናቀልን በማስከተል ስፍር ቁጥር የሌለውን ሕይወት አደጋ ላይ መጣሉን ገልጸዋል።
ሰላምን ለማስፈን የተደረጉት ሙከራዎች በሙሉ ሳይሳኩ መቅረታቸውን የተናገሩት ሚስተር ሳዲያ፥ ቀደም ብሎ በአሜሪካ እና በሳውዲ አረቢያ፣ በኋላም በግብፅ የተደረጉት የሽምግልና ጥረቶች ሳይሳኩ መቅረታቸውን አስታውሰዋል። “ከአንድ ዓመት በላይ ምንም ዓይነት ድርድር አልተደረገም” ያሉት ሚስተር ሳዲያ፥ አንዳንድ ጊዜ ጦርነቱ ለሰዓታት፣ ለቀናት ወይም ለአንድ ሳምንት ሊቆም ቢችልም ነገር ግን እንደገና እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ጦርነቱ እንደገና ባጋገረሸ ቁጥር ብዙ የሰው ሕይወት እንደሚጠፋ፣ ንብረቶች እና መሠረተ ልማቶች እንደሚወድሙ ገልጸው፥ ጦርነቱ ባስከተለው አደጋ የሱዳን ሕዝብ የመፈናቀል እና የረሃብ መከራ እንደሚፈራረቅበት አስረድተዋል።
በሰው ልጅ ላይ የደረሰ ኪሳራ
አኃዛዊው መረጃው እንደሚናገረው፥ በጦርነቱ ምክንያት ሱዳን ውስጥ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው ኪሳራ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑ ሲነገር በሴቶች እና በሕፃናት የከፋ ጉዳት መድረሱ ታውቋል። በቀውሱ ምክንያት ሕጻናት ወላጆቻቸውን፣ የትምህርት እና የወደፊት ዕድላቸውን እንዳጡ እና በሁከቱም በጣም መበሳጨታቸውን ሚስተር ሳዲያ ተናግረዋል። “ይህ ምንም አያስደንቅም” ያሉት ሚስተር ሳዲያ፥ አንዳንዶች እንደገና ጦርነቱን ሲቀላቀሉ የባሰ አስከፊ ጥቃት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸው፥ “እንደነዚህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ማንኛውም ዓይነት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቀውሱ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ልጆቻቸውን ለመንከባከብ በሚታገሉት ሴቶች ላይ ከግጭት ጋር በተያያዘ የፆታ ጥቃት ሰለባዎች እንደሚያደርጋቸው ታውቋል። “በሱዳን ባሕላዊ ደንቦች መሠረት የተጎዱ ሴቶችን ወደ ፊት ማቅረብ አስቸጋሪ ነው” ያሉት ሚስተር ሳዲያ፥ በእንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች ዙሪያ ያለውን መገለል በመግለጽ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሴቶች ለምክር አገልግሎት ወደ ድርጅታቸው እየመጡ መሆናቸውን እና የተለያዩ ድርጅቶች በአሰቃቂ ሁኔታ የተጎዱትን ሰዎች ለመፈወስ የሥነ-ልቦና ድጋፍ እንደሚሰጧቸው አስረድተዋል።
የምግብ እና የሕክምና ዕርዳታ
ሁኔታው የጨለመ፣ የጤና አጠባበቅ እጥረት እና የግብርና እንቅስቃሴ በሙሉ የወደቀ በመሆኑ ረሃብ ያንዣበበት ሲሆን፥ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሱዳን ውስጥ ዋነኛው የሞት መንስኤ እየሆነ መምጣቱ ሲነገር፥ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተዳከሙ ከመሆናቸው የተነሳ በቀላል በሽታዎች እንደሚሞቱ ታውቋል።
“ሰዎች በረሃብ እና በምግብ እጦት እየሞቱ ይገኛሉ” ያሉት ሚስተር ሳዲያ፥ የግብርና እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ በመቆማቸው ምንም ምርት እንደሌለ እና ሰዎች እርስ በርስ በመረዳዳት ላይ ቢሆኑም ነገር ግን እነዚህ የዕለት ተዕለት ፍላጎታቸውን ለማሟላት በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል። መንግሥት ቢያስተባብልም በሰሜናዊ ዳርፉር በሚገኝ የዛምዛም መጠለያ ካምፕ ረሃብ እንዳለ በይፋ መታወጁን ሚስተር ሳዲያ ገልጸዋል።
እርምጃ እንዲወሰድ የቀረበ ጥሪ
በከፍተኛ መከራ ውስጥ የሚገኝ የሱዳን ሕዝብ ተስፋውን የቆረጠ አይመስልም” ያሉት ሚስተር ሳዲያ፥ ይህም ሱዳናውያን እርስ በርስ መደጋገፋቸው እና ያላቸውን ሃብት ከመጋራቸው የሚመጣ ኃይለኛ ጥንካሬ እንደሆን አጽንኦት ሰጥተዋል።
“በግጭቱ ቢጎዱም ነገር ግን ቀጥታ ጉዳት ያልደረሰባቸው “ቀውሱ አንድ ቀን ያበቃል” ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ “ሱዳናውያን ሙሉ በሙሉ ተስፋ ባይቆርጡም ነገር ግን አንገብጋቢ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እና ሕይወታቸውን እንደገና ለማቋቋም ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሰብዓዊ ዕርዳታ ተስፋ በመቁረጥ ላይ ለሚገኙ ሰዎች የሕይወት መስመርን እንደሚፈጥርላቸው የተናገሩት ሚስተር ሳዲያ፥ “የተፈናቀሉ ሰዎች እንደ ንጹሕ ውሃ፣ የገንዘብ ድጋፍ ወይም አስፈላጊ ቁስቁሶች ዕርዳታ ሲያገኙ ተስፋን ያገኛሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
“ካፎድ” የተሰኘ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ከሌሎች የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለሱዳን ሕዝብ የሚሰጠው ድጋፍ በተጎጂው ሕዝብ መካከል ያለውን ሰብዓዊ ክብር እና ዓላማ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚረዳ ታውቋል። “ዕርዳታን መስጠት ሕይወትን ከሞት ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ሕይወትን መልሶ ማግኘት እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን ማለምለም ነው” ሲሉ ሚስተር ሳዲያ አስረድተዋል።
ለሱዳን ሕዝብ የተላከ መልዕክት
በሱዳን ሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረስ ላይ የሚገኝ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅት “ካፎድ” CAFOD ዋና ኃላፊ የሆኑት ሚስተር ቴሊ ሳዲያ፥ ለሱዳን ሕዝብ ባስተላለፉት የአብሮነት እና የማጽናናት መልዕክታቸው፥ “ቀውሱ እስኪወገድ ድረስ ሰብዓዊም ሆነ መንፈሳዊ ጥረት በማድረግ ከጎናችሁ ነን” በማለት አረጋግጠውላቸዋል።
ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበ ጥሪ
ሚስተር ቴሊ ሳዲያ፥ የጦር መሣሪያ እንጂ ምግብን ለማይልክ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው” ብለው፥ የሱዳን ችግር ዓለም አቀፋዊ ችግር መሆኑን እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ተፋላሚ ወገኖችን ትርጉም ያለው የተኩስ አቁም እና መፍትሄ እንዲገኝ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ሊያመጣቸው ይችላል” ሲሉ ተናግረው፥ ሁኔታው ከመባባሱ በፊት ቶሎ እርምጃ እንዲወሰድ” በማለት አሳስበዋል።
“በዚህ ሁሉ መካከል የቤተ ክርስቲያን ድምጽ ጸንቶ ይኖራል” ያሉት ሚስተር ቴሊ ሳዲያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለማቋረጥ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለማስፈታት ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ መልዕክታቸው እምነት እና ሕሊና ወዳላቸው ሰዎች ዘንድ ደርሶ የሰላም ጥረት እንዲያደርጉ ሊያበረታታቸው እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ “የቅዱስነታቸው መልዕክት በአመፅ ምክንያት ለሚሰቃዩት ሰዎች የቁርጠኝነት እና የተስፋ ምልክት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በ “ሰላም” ማመን
በሱዳን ያለውን ቀውስ እና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የሚከሰቱትንም ጭምር በዓይናችን እያየን ለሌሎች ስቃዮች ያለንን ግድየለሽነት እያሰብን እስከ መቼ እንዘልቃለን? የመሣሪያ ተኩስ እና የቦምብ ፍንዳታን መደበኛ ማድረግ የጀመርነው ከመቼ ነው? ልጆች ወደ ጦርነት መሄዳቸውን እና እናቶች መራባቸው ልማድ ያደረግነው ከመቼ ጀምሮ ነው? ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበለት እርምጃ አንገብጋቢ ነው፤ የሱዳናውያን ተስፋ አሁንም በሰላም የሚያምኑ ሰዎች መኖራቸውን ያስታውሰናል” ሲሉ በሱዳን ሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረስ ላይ የሚገኝ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅት “ካፎድ” CAFOD ዋና ኃላፊ የሆኑት ሚስተር ቴሊ ሳዲያ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቆይታ አጠቃለዋል።