በባንግላዲሽ ኮክስ ባዛር የሚኖሩ የሮሂንጊያ ስደተኞች በባንግላዲሽ ኮክስ ባዛር የሚኖሩ የሮሂንጊያ ስደተኞች 

በሃይማኖት ላይ የሚደርስ ስደት በሰብዓዊነት ላይ እየደረሰ የመጣ ቀውስ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በተከበረበት ኅዳር 8/2017 ዓ. ም. ድሆችን በጸሎታቸው አስታውሰው፥ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ባስተላልፉት መልዕክትም በተለያዩ ጊዜያት ሰዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት እንደሚገለሉ ገልጸው፥ ይህም በሰው ልጆች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትስስር አደጋ ላይ እንደሚጥል ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም ሰላም እንዲሰፍን በተደጋጋሚ የሚያሰሙት ድምጽ በሃይማኖታቸው ምክንያት የሚሰደዱትን በማስታወስ ሲሆን፥ ይህ አሳዛኝ ክስተት በመላው ዓለም በሚገኙ የሁሉም እምነቶች ተከታዮች ላይ እንደሚደርስ ታውቋል። ዛሬ በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኞች በእምነታቸው ምክንያት ብቻ መድልዎ፣ ጥቃት እና ሞት እንደሚደርስባቸ ታውቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደርስ ስደት
የሃይማኖት ነፃነትን የሚከታተል አንድ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን (ACN) እንዳስታወቀው፥ በዓለም ዙሪያ ከ360 ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ስደት እንደሚደርስባቸው ገልጾ፥ ይህም ጥቃትን፣ እስራትን፣ መፈናቀልን እና ሥርዓታዊ መድልዎን እንደሚጨምር አስታውቋል። ድርጅቱ በ 2023 ሪፖርቱ ከዓለም ሕዝብ መካከል ሁለት ሦስተኛው የሃይማኖት ነፃነት በተገደቡባቸው ወይም በሌለባቸው አገራት ውስጥ እንደሚኖር ገልጿል።

በናይጄሪያ እና በሕንድ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስደት
ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ከሚሰደዱባቸው አገሮች መካከል ናይጄሪያ አንዷ ስትሆን፥ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኘው ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ዒላማ በማድረግ ብዙ ጊዜ በእምነታቸው ምክንያት እንደሚያፍናቸው፣ እንደሚገድላቸው እና አብያተ ክርስቲያናትን እንደሚያወድም ታውቋል። አብዛኛው ሕዝብ የሂንዱ እምነት ተከታዮ በሆኑባት ሕንድ ውስጥ የአናሳ ሃይማኖት ተከታዮችን ስደት እንደሚደርስባቸው ታውቋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ክርስቲያኖች ስደት
ከብዙ አሥርተ ዓመታት ጀምሮ ዓመፅ በሚካሄድበት መካከለኛው ምሥራቅ በግጭት እና ስደት ምክንያት የክርስቲያኖች ቁጥር መቀነሱ ሲነገር፥ በሶርያ እና ኢራቅ ውስጥ ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት እና በጽንፈኛው እስላማዊ መንግሥት ቡድን ስጋት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ለስደት መዳረጋቸው ታውቋል። ከተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ወደ አገራቸው መመለስ ቢችሉም ያኔም ቢሆን ሕይወታቸውን መልሶ ለመገንባት ቀጣይነት ያለው ፈተና እንደሚገጥማቸው “ኦፕን ዶርስ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት በዘገባው ገልጿል።

የቤተ ክርስቲያን ሚና
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመላው የጵጵስና ዘመናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚሰደዱ ክርስቲያኖች የጸሎት እና የአብሮነት እገዛ እንዲደረግላቸው ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። በሰደት ላይ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ በማድረግ የሚታወቅ እንደ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ያሉ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፎችን በማድረግ ማኅበረሰቦችን እንደገና ለማቋቋም እና ምዕመናንን በሚያጋጥሙ ችግሮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። “አንድ የክርስቶስ አካል ሲሰቃይ ሁላችንም እንሰቃያለን” ያለው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ፥ በዓለም ዙሪያ ስደት የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ፥ በሃይማኖት ላይ የሚደርስ ስደት ክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እምነቶች እና የሰው ልጆችን የሚነካ ዓለም አቀፍ ጉዳይ መሆኑን አስረድቷል።

የሃይማኖት ነፃነትን አስመልክቶ በሰደት ላይ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ በማድረግ የሚታወቅ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ያወጣው ሪፖርት እና እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ከሌሎች የምርምር ማዕከላት እና ድርጅቶች የተገኙ ግኝቶች፣ አናሳ ሃይማኖቶች የሚደርስባቸውን ከባድ ጭቆናን ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በምያንማር የሚገኙ የሮሂንጊያ ሙስሊም ማኅበርሰብ
ከእነዚህ አናሳዎች ማኅበረሰቦች መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ በጸሎታቸው የሚያስታውሳቸው በምያንማር የሚኖሩ የሮሂንጊያ ሙስሊም ማኅበርሰብ አንዱ እንደሆነ ታውቋል። በምያንማር መንግሥት ሀገር አልባ ተብለው የተፈረጁት የሮሂንጊያ ማኅበረሰቦች የሥርዓት አድልዎ ሰለባ ሲሆኑ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 የምያንማር ጦር በሮሂንጊያ ማኅበረሰቦች ላይ በወሰደው የኃይል እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ ከ 700,000 በላይ ሰዎች ወደ ጎረቤት ባንግላዲሽ መሰደዳቸውን ተከትሎ ሁኔታው መባባሱ ታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ይህ የጅምላ ግድያ ዘመቻ ጾታዊ ጥቃትን በማድረስ መንደሮችን በሙሉ ማውደሙ ይታወሳል። ይህ ጥቃት ዓለም አቀፍ ውግዘት ቢደርስበትም ሮሂንጊያዎች የዜግነት፣ የትምህርት እና እምነታቸውን የመለማመድ ነፃነትን ጨምሮ መሠረታዊ መብቶችን ተነፍገው መቆየታቸው ታውቋል። የምግብ፣ የጤና አጠባበቅ እና የደህንነት አቅርቦት ውስን በሆነባቸው በተጨናነቀ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እየኖሩ የማያቋርጥ የጥቃት ዛቻን እየተጋፈጡ እንደሚገኙ ታውቋል።

በምያናማር ውስጥ በሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለው ስደት ያልተነገረለት ጭካኔ የተሞላበት የሃይማኖት ስደት ቢሆንም ሌሎች አናሳ ሃይማኖቶችም በአክራሪ መንግሥታት በሚፈጸምባቸው ጥቃት እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ታውቋል። በአፍጋኒስታን ምንም እንኳን ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ቢሆንም ሂንዱዎች እና የሲክ እምነት ተከታዮች በጽንፈኛ ቡድኖች በሚደርስባቸው ዛቻ ምክንያት ከሀገር ለመሰደድ መገደዳቸው ታውቋል።

ለህሊና የቀረበ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መሪነታቸው “በማኅበረሰቡ ለተገለሉት የሚደርሱ” የሚል ስም የተሰጣቸው መሆኑን ቤተ ክርስቲያን በማስታወስ፥ ቅዱስነታቸው “ሁላችንም የአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት ነን” በሚለው አቋማቸው እምነታቸው ምንም ይሁን ምን በዓለም ዙሪያ ፍትሕ የጎደለባቸውን እና ማንኛውም ዓይነት ስቃይ የሚደርስባቸውን ሕዝቦች በጸሎታቸው በማስታወስ ያላቸውንም ቅርበት ዘወትር እንደሚገልጹ በማስታወስ በዓለም ዙሪያ ለሃይማኖት ነፃነት በሚደረግ ትግል በጽናት መቆሟን አስታውቃለች።

 

 

18 November 2024, 16:28