ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ እግዚአብሔርን መገናኘት ማለት ፍቅር ማግኘት ማለት ነው አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በእለቱ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ቃል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 09/2013 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከዮሐንስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበውና “ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ! የእግዚአብሔር በግ” አለ።ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት” (ዮሐንስ 1፡35-41) በሚለው ስለመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በምያወሳው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን እግዚአብሔርን መገናኘት ማለት ፍቅር ማግኘት ማለት ነው ማለታቸው ተገልጿል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በእዚህ መደበኛ ሁለተኛ እለተ ሰንበት የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 1፡35-42) የኢየሱስን የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት ያመለክታል። ግንኙነቱ የተከናወነበት ቦታ ኢየሱስ በተጠመቀ ማግስት በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ ነበር። ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ! የእግዚአብሔር በግ” አለ (ዮሐንስ 1፡36)። እነዚያ ሁለቱ በመጥምቁ ምስክርነት ታምነው ኢየሱስን ተከትለው ሄዱ። ኢየሱስም ይህንን በመገንዘቡ የተነሳ “ምን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው “መምህር ሆይ የት ነው የምትኖረው?” (ዮሐንስ 1፡38) ብለው ጠየቁት።
ኢየሱስ “እኔ በቅፍርናሆም ወይም በናዝሬት ውስጥ እኖራለሁ” ብሎ አልመለሰም ፣ ነገር ግን እርሱም “ኑና እዩ” አላቸው (ዮሐንስ 1፡39)። ይህ ደግሞ እንዲያው በቀላሉ መጥተው እንዲጎበኙ ለማደረግ የቀረበ የጥሪ ካርድ ሳይሆን ነገር ግን ከእርሱ ጋር እንዲገናኙ የቀረበ ግብዣ ነው። ሁለቱም ይከተሉታል እናም ያን ቀን ከሰዓት በኋላ አብረውት ይቆያሉ፣ በጌታ ፊት ቁጭ ብለው ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ጌታ በሚናገርበት ጊዜ የልባቸው ሙቀት እየጨመረ እንደሄደ መገመት አያስቸግርም። ለታላቁ ተስፋቸው ምላሽ የሚሰጡ የቃላት ውበት ይሰማቸዋል። እናም በድንገት ፣ ዙሪያቸው ሲጨልም ፣ በውስጣቸው፣ በልባቸው ውስጥ፣ እግዚአብሔር ብቻ ሊሰጥ የሚችለው ብርሃን ይፈነጥቃል። ትኩረትን የሚስብ አንድ ነገር ይከሰታል -ከመካከላቸው አንዱ ከስልሳ ዓመታት በኋላ ወይም ምናልባትም ከዚያ በላይ በኋላ በጻፈው ወንጌል ላይ “ከቀኑም ዐሥር ሰዓት ያህል ነበር” (ዮሐ 1፡39) በማለት ጽፏል። እናም ይህ እንድናስብ የሚያደርገን ነገር ነው -ከኢየሱስ ጋር የሚደረግ እያንዳንዱ እውነተኛ ገጠመኝ በሕያው ትውስታ ውስጥ ይቆያል ፣ መቼም አይረሳም። በጣም ብዙ ገጠመኞችን እንረሳለን፣ ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር ያለው እውነተኛ ገጠመኝ ሁል ጊዜም ከእኛ ጋር አብሮ ይኖራል። እናም እነዚህ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ከብዙ ዓመታት በኋላም እንኳን እንዲሁ ሰዓቱን አስታወሱ፣ ህይወታቸውን የቀየረ አጋጣሚ በመሆኑ ይህን አስደሳች፣ ምልአት ያለው ግንኙነት መዘንጋት አልቻሉም ነበር። ከዚያም በኋላ ከዚህ ግንኙነት በኋላ ወደ ወንድሞቻቸው ሲመለሱ ይህ ደስታ ፣ ይህ ብርሃን ከልባቸው ሞልቶ እንደ ሚፈስ ወንዝ በመሆን እንደ ጎርፍ መፍሰስ ይጀምራል። ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱ እንድርያስ ለወንድሙ ለስምዖን - ኢየሱስ በኋላ ሲገናኘው ጴጥሮስ ብሎ ይጠራዋል - “መሲሑን አገኘነው” (ዮሐንስ 1፡41) በማለት ይነግረዋል። እነሱ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን እርግጠኛ ሆነዋል ፣ እርግጠኛም ነበሩ።
ከእርሱ ጋር ለመሆን ከሚጠራው ከክርስቶስ ጋር መገናኘት እንዳለብን በምያመለክተው በዚህ ገጠመኝ ላይ ለአፍታ ቆም እንበል። እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ጥሪ የእርሱ የፍቅሩ ተነሳሽነት ነው። ቀድሞ ተነሳሽነቱን የሚወስደው እርሱ ነው፣ እርሱ ይጠራናል። እግዚአብሔር ወደ ሕይወት ይጠራል ፣ ወደ እምነት ይጠራል እናም ወደ አንድ የተወሰነ የሕይወት ሁኔታ ይጠራል “እኔ እዚህ ቦታ እንድትገኝ እፈልጋለሁ” በማለት ይጠራናል። የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ጥሪ እርሱ ሕይወት እንድናገኝ ያቀረበልን የሕይወት ጥሪ ሲሆን ይህም የግለሰብ ጥሪ ነው ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር በተከታታይ ነገሮችን አያደርግም። ያኔ እግዚአብሔር እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ወደ እምነት እና የቤተሰቡ አካል እንድንሆን ይጠራናል፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔር ወደ አንድ የተወሰነ የሕይወት ሁኔታ ይጠራናል -በጋብቻ መንገድ ፣ በክህነት ወይም በተቀደሰ ሕይወት ውስጥ እራሳችንን እንድንሰጥ ይጠራናል። እነሱ የእግዚአብሔር እቅድ ለማከናወን የተለያዩ መንገዶች ናቸው፣ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያለው፣ እሱም ሁል ጊዜም የፍቅር እቅድ ነው። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይጠራል። እናም ለእያንዳንዱ አማኝ ትልቁ ደስታ ለዚህ ጥሪ ምላሽ መስጠት ፣ ለእግዚአብሄር እና ለወንድሞቹ አገልግሎት እራሱን መስጠት ነው።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ በሺዎች በሚቆጠሩ መንገዶች እና በሰዎች በኩል ሊደርሰን ከሚችለው የጌታ ጥሪ ጋር ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች ሊከሰቱ የሚችሉ ሲሆን በደስታ እና አሳዛኝ ክስተቶች ፣ አንዳንድ ጊዜ አመለካከታችን ውድቅ ሊሆን ይችላል - "አይ ... እፈራለሁ ... - ፣ በማለት የቀረበልንን ጥሪ ውድቅ የምናደርግ ሲሆን ከምኞታችን በተቃራኒው የሚገኙ ሲሆኑ ወይም ደግሞ እንዲሁም በፍርሃት፣ ምክንያቱም እኛ በጣም አስፈላጊ እና የማይመች አድርገን ስለቆጠርነው “ኸረ እኔ አላደርገውም፣ የተሻለ አይደለም ፣ እግዚአብሄር እዚያ ፣ እኔ እዚህ የተሻለ ሰላማዊ ኑሮ መኖር ይሻለኛል…” በማለት የጌታን ጥሪ ውድቅ እናደርገዋለን። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ፍቅር ነው ፣ ከእያንዳንዱ ጥሪ በስተጀርባ ያለውን ፍቅር ለማግኘት መሞከር አለብን ፣ እኛም ለእርሱ ምላሽ የምንሰጠው በፍቅር ብቻ ነው። ይህ ቋንቋ ነው ከፍቅር ለሚመጣ ጥሪ መልሱ ፍቅር ብቻ ነው። መጀመሪያ ላይ አንድ ገጠመኝ አለ ፣ በእርግጥ ስለ አብ የሚናገርልንን ፍቅሩን እንድናውቅ ከሚያደርገን ከኢየሱስ ጋር መገናኘት አለ። እናም እኛ የምንወዳቸው ሰዎችን በራስ ተነሳሽነት ለማወጅ ፍላጎት በእኛም ውስጥ እንዲነሳሳ ያደርጋል። “ፍቅርን አገኘሁ” ፣ “መሲሑን አገኘሁ” ፣ “እግዚአብሔርን አገኘሁ” ፣ “ኢየሱስን አገኘሁ” ፣ “የእኔን የሕይወት ትርጉም አገኘሁ " በማለት በድፍረት መናገር እንችላለን። በአንድ ቃል “እግዚአብሔርን አግኝቻለሁ” ማለት እንችላለን። በጥሪው ምላሽ፣ በትህትና እና በደስታ የፍቃዱ ፍፃሜ በሕይወታችን ለእግዚአብሄር የውዳሴ መዝሙር ለማድረግ ድንግል ማርያም ትረዳን። ግን ይህንን እናስታውስ - ለእያንዳንዳችን ፣ በህይወት ውስጥ ፣ እግዚአብሄር በጥንካሬ እራሱን በበለጠ አጥብቆ የሚያቀርብበት አንድ ጊዜ ነበር። እስቲ እናስታውሰው። ወደዚያ ጊዜ እንመለስ ፣ የዚያ ቅጽበት መታሰቢያ ከኢየሱስ ጋር ስንገናኝ ሁል ጊዜ ያድሰናል።