ምዕመናን በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ምዕመናን በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቡርኪና ፋሶ የተፈጸመውን ደም ማፍሰስ አውግዘው የሰላም ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቡርኪና ፋሶ ውስጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በአንድ መስጊድ ላይ አሸባሪዎች በፈጸሙት ጥቃት በተገደሉት ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ የአምልኮ ቦታዎች እንዲከበሩ እና የሕዝቡ የሰላም እሴት እንዲጎለብት ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቡርኪና ፋሶ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ኤሳካኔ ውስጥ አሸባሪዎች እሁድ የካቲት 17/2016 ዓ. ም. በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ በነበሩት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።“አሳዛኝ የአሸባሪዎች ጥቃት” በተባለው በዚህ አደጋ፥ በአንድ መስጊድ ውስጥም ለጠዋት ጸሎት በተሰበሰቡበት ሙስሊም ምእመናን ላይ በተፈፀመው ግድያ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል በላኩት የቴሌግራም መልዕክታቸው፥ ጥላቻ ለግጭት መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ያላቸውን ጽኑ እምነት በድጋሚ ገልጸዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ፍራንችስኮስ የአጋርነት መልዕክት ምዕመናኑን የደረሳቸው፥ በምዕራብ የአፍሪቃ አገር ቡርኪና ፋሶ ውስጥ በምትገኝ የኤስካኔ ካቶሊክ ማኅበረሰብ ላይ ባለፈው እሁድ በተፈጸመው ጥቃት 15 ምእመናን በተገደሉበት ወቅት ሲሆን፥ ታጣቂ አሸባሪዎች በተመሳሳይ ዕለትም ናቲያቦኒ በተባለ የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኘው አንድ መስጊድ ላይ ሌላ ጥቃት ፈጽመው በደርዘን የሚቆጠሩትን ገድለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ፍራንችስኮስ፥ የቡርኪና ፋሶ እና የኒጀር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ለሆኑት ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ሎረን ዳቢሬ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፥ በጥቃቱ ለደረሰው የሕይወት መጥፋት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ የቤተሰቦቻቸውን ሐዘን እንደሚጋሩት እና ለሞቱት ነፍሳት የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ለቆሰሉትም የእርሱን ፈውስ በጸሎታቸው ለምነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ ጥላቻ ለግጭቶች መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል በማስታወስ፥ ቅዱሳት ሥፍራዎች እንዲከበሩ እና የሰላም እሴቶችን ለማጎልበት ዓመፅን መዋጋት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ለቡርኪና ፋሶ ሕዝብ እና ለመላዋ አገሪቱ መለኮታዊ ቡራኬን በመላክ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

27 February 2024, 15:25