ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ቅዱስ ቁርባን በአዲሱ ዓለም ውስጥ ነቢያት እንድንሆን ያደረጋናል ማለታቸው ተገለጸ!
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!
ዛሬ በጣሊያን እና በሌሎች አገሮች የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደሙ የሚከበርበት በዓል ነው። በዛሬ ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ስለ መጨረሻው እራት ይነግረናል (ማር. 14፡12-26)። በዚህ ጊዜ ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረውን የመጨረሻ ሰሞን ግንኙነት ሲፈጽም፡ እንደውም በተቆረሰው ኅብስትና ለደቀ መዛሙርቱ በሚቀርበው ጽዋ ውስጥ ነው። ለሰው ልጆች ሁሉ ራሱን የሰጠ እና እራሱን ለዓለም ህይወት የሚሰጥ እርሱ ነው።
እንጀራውን በሚቆርስበት የኢየሱስ ትይንት ውስጥ ቅዱስ ወንጌሉ አጽንዖት የሚሰጠው “ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው” (ማርቆስ 14፡ 22) በሚለው ቃል ውስጥ የሚያጎላ አንድ አስፈላጊ ገጽታ አለ። እነዚህን “ቆርሶ ሰጣቸው” የሚሉትን ቃላት በልባችን ውስጥ እናጽናቸው። በእርግጥም ቅዱስ ቁርባን በመጀመሪያ የስጦታውን ግዝፈት ያስታውሳል። ኢየሱስ ኅብስቱን የወሰደው በራሱ ሊበላ ሳይሆን ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሊሰጥ ነው፣ ስለዚህም ማንነቱንና ተልእኮውን ገለጠ። ሕይወቱን ለራሱ አላዘጋጀም፣ ነገር ግን ሕይወቱን ለሌላ ሰጠ፥ የእርሱን ማንነት እንደ እግዚአብሔር በቅናት የተያዘ ውድ ሀብት አድርጎ አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የእኛን ስብዕና ለመካፈል ክብሩን ገፍፎ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት እኛ እንድንገባ ራሱን ዝቅ አደረገ (ፊልጵ. 2፡1-11)። ኢየሱስ መላ ሕይወቱን ስጦታ አድርጎ ሰጥቶናል። እስቲ ይህን እናስታውስ፡ ኢየሱስ መላ ሕይወቱን ስጦታ አድርጎ ሰጥቷል።
እንግዲያውስ በተለይ እሁድ እንደምናደርገው መስዋዕተ ቅዳሴን ማስቀደስ እና ይህን እንጀራ መብላት ከሕይወት የራቀ አምልኮ ወይም የግል መጽናኛ ጊዜ እንዳልሆነ እንረዳ። ኢየሱስ ኅብስቱን እንደወሰደ፣ ቆርሶ እንደ ሰጣቸው ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን፣ ስለዚህም ከእርሱ ጋር መገናኘታችን ለሌሎች የተሰበረ እንጀራ እንድንሆን ያደርገናል፣ ማንነታችንን እና ያለንን ለመካፈል ይረዳናል። ታላቁ ቅዱስ ሊዮ እንዲህ አለ፡- ‘በክርስቶስ ሥጋና ደም ውስጥ ያለን ተሳትፎ የምንበላውን እንድንሆን ያደርገናል’ ማለታቸው ይታወሳል።
ወንድሞች እና እህቶች፣ የተጠራንለት ይህ ዓላማ ይህ ነው፤ የምንበላውን እንድንሆን፣ “ቅዱስ ቁርባን” እንድንሆን፣ ማለትም፣ ከእንግዲህ ለራሳችን የማንኖር ነገር ግን ለሌሎች የምንኖር ሰዎች እንድንሆን ተጠርተናል (ሮሜ 14፡7)፣ በሐብት ይዞታ አመክንዮ የፍጆታ እቃዎችን በማግበስበስ ሳይሆን የራሳቸውን ሕይወት ለሌሎች እንዴት ስጦታ ማድረግ እንደሚችሉ የሚያውቁ ሰዎች እንድንሆን ነው የተጠራነው፣ አዎን ለእዚህ ነው የተጠራነው። በዚህ መንገድ ለቅዱስ ቁርባን ምስጋና ይግባውና ነብያት እና የአዲስ ዓለም ገንቢዎች እንሆናለን፡ ራስ ወዳድነትን አሸንፈን ለፍቅር ራሳችንን ስንከፍት የወንድማማችነትን ትስስር ስንፈጥር፣ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ስቃይ ውስጥ ራሳችንን አስገብተን እና የሥቃያቸው ተካፋይ ሆነን ከተካፍለን ከተቸገሩት ጋር እንጀራ እና ሃብት፣ መክሊታችንን ሁሉ ስንካፈል፣ ያኔ የህይወታችንን እንጀራ እንደ ኢየሱስ እየቆረስን ነው ለማለት እንችላለን።
ወንድሞች እና እህቶች፣ እራሳችንን እንጠይቅ፡ ሕይወቴን ለራሴ ብቻ ነው የምኖረው ወይስ እንደ ኢየሱስ ነው የምሰጠው? ራሴን ለሌሎች አሳልፌ ሰጣለሁኝ ወይንስ በራሴ ትንሽነት ውስጥ ራሴን ዝግቼ ኖራለሁ? እናም በዕለት ተዕለት ሁኔታዎች፣ እንዴት ማካፈል እንዳለብኝ አውቃለሁ ወይስ ሁልጊዜ የራሴን ፍላጎት እፈልጋለሁ?
ከሰማይ የወረደውን የሕይወት እንጀራ የሆነውን ኢየሱስን የተቀበለች እና ራሷን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ የሰጠች ድንግል ማርያም እኛንም በቅዱስ ቁርባን ከኢየሱስ ጋር አንድ በመሆን የፍቅር ስጦታ እንድንሆን በአማላጅነቷ ትርዳን።