ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ኢየሱስን በእውነት ስናውቅ ሁሉም ነገር ይለወጣል” ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ መስከረም 6/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በ ዕለቱ ባሰሙት ስብከት፥ “ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት ስናውቅ ሁሉም ነገር ይለወጣል” ሲሉ አስገንዝበዋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን የቅዱስነታቸውን አስተንትኖ ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከማር. 8: 27-35 ተወስዶ የተበበው የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሕዝቡ እርሱን ማን እንደሚያሉት ከጠየቃቸው በኋላ፥ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ያቀረበላቸውን ጥያቄ ያስታውሰናል። (ማር. 8:29) ጴጥሮስም ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ወክሎ እንዲህ ሲል መለሰ። ‘አንተ ክርስቶስ ነህ፤ አንተ መሲህ ነህ ሲል’ መለሰ (ቁ. 8:30)። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ስለሚጠብቀው ሥቃይ እና ሞት መናገር ሲጀምር ይኸው ጴጥሮስ በመቃወሙ ‘አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔር ነገር አታስብምና’ በማለት አጥብቆ ገሠጸው። (ቁ. 33)


እኛም የሐዋርያው ጴጥሮስን አመለካከት ስንመለከት ኢየሱስን በትክክል ማወቅ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ኢየሱስን ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው? በእርግጥ በአንድ በኩል ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመንገሩ ፍጹም ትክክል መልስ ሰጥቷል። ሆኖም ከዚህ ትክክለኛ መልስ በስተጀርባ አሁንም ሰብዓዊ አስተሳሰብ አለ። እሱም ጠንካራ መሲህ መሆኑን፣ አሸናፊ መሲህ መሆኑን፣ ሊሰቃይ ወይም ሊሞት የማይችል መሆኑን የሚገልጽ አስተሳሰብ ነው። ስለዚህ ጴጥሮስ የመለሰው መልስ ትክክል ነው። ነገር ግን የአስተሳሰብ መንገዱ አልተለወጠም። አሁንም አስተሳሰቡን መቀየር አለበት።

ይህ መልዕክት ለእኛም ጠቃሚ ነው። በእርግጥ እኛም ስለ እግዚአብሔር ማንነት አንድ ነገር ተምረናል። የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎችንም እናውቃለን፤ ጸሎቶችንም በትክክል እንደግማለን። ምናልባትም ‘ኢየሱስ ለአንተ ወይም ለአንቺ ማን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ ከትምህርተ ክርስቶስ የተማርናቸውን አንዳንድ ትምህርቶች በማስታወስ ጥሩ መልስ እንሰጥ ይሆናል።

ነገር ግን ይህ መልሳችን ኢየሱስ ክርስቶስን በትክክል እናውቃለን ለማለት ያስችለናል? እንደ እውነቱ ከሆነ ኢየሱስን ማወቅ ወይም ስለ እርሱ አንድ ነገር ማወቅ ብቻው በቂ አይደለም። ይልቁንም እሱን መከተል፣ በወንጌሉ መነካት እና መለወጥ ያስፈልጋል። ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠርን ይጠይቃል። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ነገሮችን ማወቅ እችላለሁ። ነገር ግን ከእርሱ ጋር ካልተገናኘን ኢየሱስ ማን እንደሆነ አናውቅም። ኢየሱስን በትክክል ማወቅ ሕይወትን ይቀይራል። ማንነትን ይለውጣል፤ የአስተሳሰብ መንገድን ይቀይራል፤ ከወንድሞች እና ከእህቶች ጋር ያለንን ግንኙነት ይለውጣል፤ እንደማንነታቸው ለመቀበል እና ይቅር ለማለት ፈቃደኞች ያደርገናል። የሕይወት ምርጫንም ጭምር ይለውጣል። ኢየሱስን በእውነት ወደ ማወቅ ከደረስን ሁሉም ነገር ይለወጣል!

የናዚ አገዛዝ ሰለባ እና የሉተራን ሃይማኖት ምሁር እና መጋቢ ቦንሆፈር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- ‘ያለማቋረጥ የሚያስጨንቀኝ ነገር ቢኖር፥ ክርስትና ዛሬ ለእኛ ምንድን ነው? ወይም ክርስቶስ ማን ነው’ የሚለው ጥያቄ ነው” አለመታደል ሆኖ ብዙ ሰዎች ይህንን ጥያቄ ለራሳቸው አያቀርቡም፤ ምንም አያስጨንቃቸውም፣ እንቅልፍ ውስጥ ይገኛሉ። ከእግዚአብሔርም እንደ ራቁ ይቆያሉ። ይልቁንስ ኢየሱስ ለእኔ ማን ነው? በሕይወቴ ውስጥ ምን ቦታ አለው? ዓለማዊ አስተሳሰብ ይዤ ኢየሱስን በቃል ብቻ እከተላለሁ? ወይንስ ከእርሱ ጋር በመገናኘት እና ሕይወቴን እንዲለውጥ በመፍቀድ እርሱን ለመከተል ተነስቻለሁ? ብሎ እራስን መጠየቅ አስፈላጊ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርበት የምታውቅ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትረዳን።”
 

16 September 2024, 17:12