ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር ሲገናኙ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ቤተ ክኅነት በቲሞር-ሌስቴ የክርስቶስ መዓዛ ናቸው” በማለት ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር-ሌስቴ መዲና ዲሊ ውስጥ በማድረግ ላይ በሚገኙት ሐዋርያዊ ጉብኝት በከተማዋ የሚገኘውን የኢርማስ አልማ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት የሚስዮን ትምህርት ቤትን ከጎበኙ በኋላ፥ በንጽሕ እመቤታችን ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ ከአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በመሆን ጸሎት አድርሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዲሊ በሚገኘው የንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ለተሰበሰቡ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ባደረጉት ንግግር የወንጌልን መዓዛ በቲሞር-ሌስቴ እንዲይዙት እና እንዲያሰራጩ አሳስበው፥ ምክንያቱም ቲሞር-ሌስቴ በዓለም ጫፍ እና በወንጌል ልብ የምትገኝ አገር ስለሆነች ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምሥራቅ ቲሞር ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ባደረጉት ንግግር ቲሞር-ሌስቴ ምንም እንኳን በዓለም የኤኮኖም ዕድገት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ብትሆንም በተለይ በድኅነት የሚቸገሩ ሰዎችን የሚያተኩር የወንጌል ማዕከላዊ ሥፍራ እንደሆነች አመልክተዋል።


በምድር ዳርቻ የምትገኝ ማዕከላዊ የወንጌል ክፍል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቲሞር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት አቡነ ኖርቤርቶ ዶ አማራል የመግቢያ ንግግር በመነሳት፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ የተገለሉት እና የተናቁት ማዕከላዊ ሥፍራ እንዳላቸው እናውቃለን” ብለዋል።

አንዲት ገዳማዊ እህት፣ አንድ ካኅን እና አንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር ባካፈሉት ምስክርነት ላይ በማሰላሰል ንግግር ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከዮሐንስ ወንጌል በተወሰደው እና የቢታንያ ማርያም የኢየሱስን እግር በውድ ሽቶ የቀባችውን ታሪክ አስታውሰዋል።

“ይህ ታሪክ እኛ የክርስቶስን እና የወንጌሉን መዓዛ እንድንጠብቅ እና እንድናስፋፋ የተጠራን መሆናችንን ይነግረናል” ብለው፥ በክልሉ የሚገኘውን የሰንደል እንጨት ዘይቤን በመጠቀም፥ የቲሞር ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በቲሞር-ሌስቴ የክርስቶስ መዓዛ መሆናቸውን ተገንዝበው ወደ እምነታቸው ምንነት እንዲመለሱ አሳስበዋቸዋል።

የወንጌልን መዓዛ መጠበቅ እና ባሕልን ማጽዳት
“የወንጌል መዓዛ ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን የክርስቶስን እግር ለመቀባት፣ ወንጌልን ለመመስከር እና ድሆችን ለማገልገል” መሆኑንም ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። በተጨማሪም ከክርስቲያናዊ ትምህርቶች ጋር ሊጋጩ ከሚችሉ ጥንታዊ እና አንዳንዴም አጉል ከሆኑ እምነቶች እና ልማዶች ባሕላቸውን ለማንጻት እንዲረዳቸው የክርስትና ትምህርት እና እምነት ያለማቋረጥ ማደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሌላ በኩልም በትንሣኤው ማመን እና የሙታንን ነፍስ እንደ ማክበር የመሳሰሉ አንዳንድ ውብ ባሕላቸውን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ አበረታተዋቸዋል።

ወንጌልን ማስፋፋት
ቅዱስነታቸው በመቀጠል በቲሞር-ሌስቴ የሚገኙት ቀሳውስት እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የወንጌልን መዓዛ በቅንዓት እና በድፍረት እንዲያሰራጩ እና የሚስዮናዊነት መንፈስ እንዲቀበሉ አደራ ብለዋል። የቲሞር ሕዝብ ከዓመታት ጦርነት በኋላ እርቅን፣ ሰላምን፣ ርኅራኄን እና ፍትሕን እንዲያጎለብት፣ ከረጅም የክርስትና ታሪክ ሥር በመስደድ በሀገሪቱ ውስጥ ለወንጌል አገልግሎት እንደገና መነሳሳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ዓመፅን እና ድህነትን ለመዋጋት የሚያስችል የታደሰ የወንጌል መነሳሳት
የወንጌል መዓዛ ድሆች በእግራቸው እንዲቆሙ የሚረዳ፣ የምሥራቅ ቲሞር ማኅበረሰብን የሚጎዱ እንደ ዓመፅ፣ የአልኮል ሱሰኝነት እና የሴቶችን ክብር የሚያጎድሉ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመዋጋት የሚያስችል የርኅራኄ መዓዛ በመሆኑ መስፋፋት አለበት ብለዋል።

“የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አዲስ ማኅበረሰብ የመፍጠር ኃይል አለው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ለዚህም ቲሞር-ሌስቴ ቅንዓት ያለው፣ ዝግጁ እና አሳቢ ቀሳውስት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ያስፈልጓታል” ብለዋል።

ካኅናት የእግዚአብሔር ምሕረት ምልክት መሆን አለባቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይ ካህናትን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ካኅናት ትሑት ሆነው እንዲቀጥሉ እና ሚናቸውን ለግል ጥቅም ወይም ክብር እንዳይጠቀሙ አሳስበው፥ በአገልግሎታቸው ዘወትር ሰዎችን መባረክ እና ማጽናናት እንዳለባቸው፣ የርኅራኄ አገልግሎት እና የእግዚአብሔር ምሕረት ምልክት እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲደመድሙ፥ እግዚአብሔር የጠራቸውን እና የላካቸውን እንዴት መንከባከብ እንደሚገባ ያውቃል” በማለት የአባ ሳንቾ ምስክርነትን ለታዳሚው አስታውሰዋል።

 

10 September 2024, 17:41