ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "እውነተኛ ፍቅር በእግዚአብሔር መወደድ ላይ መሠረቱን ያደረገ ነው" አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
"የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማር. 10፣ 17-30) ኢየሱስን አግኝቶ 'ቸር መምህር ሆይ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ማድረግ ይገባኛል?' ብሎ ስለጠየቀው አንድ ሀብታም ሰው ይነግረናል። ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ትቶ እንዲከተለው ጋብዞታል፤ ነገር ግን ሰውዬው አዝኖ ሄዷል፤ ምክንያቱም ጽሑፉ እንደሚለው፥ 'ብዙ ንብረት ነበረው' (ማር 10፡ 23)። ሁሉንም ነገር መተው ዋጋ ያስከፍላል።
የዚህን ሰው ሁለት እንቅስቃሴዎች እናያለን:-በመጀመሪያ ላይ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ ይሮጣል፥ በመጨረሻ ግን አዝኖ ይሄዳል፣ በጣም ያዝናል። መጀመሪያ ወደ እሱ እየሮጠ ይሄዳል፣ ከዚያም አዝኖ ወደ ኋላ ይመለሳል። በዚህ ላይ እናተኩር።
በመጀመሪያ ይህ ሰው እየሮጠ ወደ ኢየሱስ ሄደ። በልቡ ውስጥ የሆነ ነገር የሚገፋፋው ያህል ነው። በእውነቱ ምንም እንኳን ብዙ ሀብት ቢኖረውም እርካታ አላገኘም፤ የውስጥ እረፍት ማጣት ይሰማዋል፤ የተሟላ ሕይወት ይፈልጋል። ሕመምተኞችና በደዌ የተለከፉ ሰዎች ብዙ ጊዜ እንደሚያደርጉት (ማር. 3:10፤ 5:6) ይህንን በወንጌል ውስጥ እናያለን፤ ራሱን ከጌታው እግር ሥር ይጥላል። እርሱ ሀብታም ሰው ነው፤ ነገር ግን ፈውስ ያስፈልገዋል። ሀብታም ነው ግን መፈወስ ያስፈልገዋል። ኢየሱስ በፍቅር ያየዋል (ማር 10፡ 21)፣ ከዚያም “ህክምና” ያቀርብለታል። ያለውን ሁሉ ለመሸጥ፣ ለድሆች ለመስጠት እና እሱን ለመከተል የሚያስችል ሕክምና ያቀርብለታል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ያልተጠበቀ መደምደሚያ ይመጣል፤ ይህ ሰው ፊቱን ጥሎ ይሄዳል! ከኢየሱስ ጋር ለመገናኘት የነበረው ፍላጎት በጣም ታላቅ እና ግትር ነበር፤ ስንብቱ ምን ያህል ቀዝቃዛ እና ፈጣን ነበር።
እኛ ደግሞ በልባችን ውስጥ የማይሻር የደስታ ፍላጎት እና ትርጉም ያለው ሕይወት እንፈልጋለን። ነገር ግን መልሱ የሚገኘው በቁሳዊ ነገሮች እና በምድራዊ ደህንነቶች ውስጥ ነው ብለን በማሰብ ልንወድቅ እንችላለን። ይልቁኑ ኢየሱስ ወደ ምኞታችን እውነት ሊመልሰንና፣ በእውነቱ፣ የምንመኘው ቸርነት እግዚአብሔር ራሱ፣ ለእኛ ያለው ፍቅር እና እርሱ እና እርሱ ብቻ ሊሰጠን የሚችለው የዘላለም ሕይወት መሆኑን እንድናውቅ ሊያደርገን ይፈልጋል። እውነተኛው ሀብት በጌታ ፍቅር መታየት አለበት፤ ይህ ትልቅ ሀብት ነው፤ እና ኢየሱስ ከዚያ ሰው ጋር እንዳደረገው ህይወታችንን ለሌሎች ስጦታ በማድረግ እርስ በርስ ለመዋደድ ያለንን ፍላጎት ማሳደግ አለብን። ወንድሞች እና እህቶች! ስለዚህ ኢየሱስ ለስጋት እንድንጋለጥ፣ ፍቅርን እንድንጋፈጥ ይጋብዘናል። ሁሉንም ነገር ለድሆች ለመስጠት እንድንሸጥ ማለትም ከራሳችን እና ከውሸት ደህንነታችን አውጥተን ለተቸገሩ ሰዎች እንድንሰጥ እና እራሳችንን በትኩረት እንድንከታተል ይጋብዘናል። ንብረታችንን ማካፈል ነገሮችን ብቻ ሳይሆን እኛ የሆንነውን፣ ችሎታችንን፣ ጓደኝነታችንን፣ ጊዜያችንን.. ወዘተ እንድናካፍል ይጠይቀናል።
ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! ያ ሀብታም ሰው ራሱን ሥጋት ላይ መጣል አልፈለገም፤ የምን ሥጋት? ፍቅርን ስጋት ላይ መጣል አልፈለገም፤ እናም በሐዘነ መንፈስ ተመልሶ ሄደ። እኛስ? ልባችን ከምን ጋር ተጣብቋል? የህይወት ረሃባችንን እና ደስታን እንዴት እናርካው? ለድሆች፣ በችግር ውስጥ ላሉ ወይም መደመጥ ለሚያስፈልጋቸው፣ ፈገግታ፣ ቃልን መልሶ ተስፋ እንዲያደርጉ መርዳትን እናውቃለን? መደመጥ ያለበት ማን ነው? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ።… ይህንን እናስታውስ፤ እውነተኛው ሀብት የዚህ ዓለም ሀብት አይደለም፤ እውነተኛው ሀብት በእግዚአብሔር መወደድ እና እንደ እርሱ ሌሎችን መውደድን መማር ነው።
የሕይወት ሃብት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ ትረዳን ዘንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንለምን።"