ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ በእምነትና በተስፋ ወደ ኢየሱስ ተመለሱ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ስርዓተ አምልኮ ላይ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደምያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 17/2017 ዓ.ም ያደርጉት አስተንትኖ " ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን ፈወሰ" (ማር. 10፡46-52) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በእምነትና በተስፋ ወደ ኢየሱስ ተመለሱ ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል ተከተታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!

በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማር 10፡46-52) ኢየሱስ አንድ ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው እንዴት እንደ ፈወሰ ይነግረናል። ስሙ በርጤሜዎስ ይባላል፥ ነገር ግን በጎዳና ላይ ያሉት ሰዎች ችላ ይሉት ነበር፡ እሱ ምስኪን የእኔ ቢጤ (ለማኝ) ሰው ነበር። እነዚያ ሰዎች ዐይነ ሰውር የነበረውን ሰው የሚመለከት ዓይን አልነበራቸውም ነበር፥ ትተውታል፣ ቸል ብለውታል። አሳቢ እይታ የለም ፣ የርህራሄ ስሜት የለም። በርጤሜዎስም አላየም፣ ግን ሰምቶ ራሱን አሰማ። “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ማረኝ!” እያለ ይጮኻል። (ማር. 10፡48) ኢየሱስ ግን ሰምቶ ያየዋል። ኢየሱስ እራሱን ለእርሱ ቅርብ እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። (ማር 10፡51)

"ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?" ይህ ጥያቄ፣ ዓይነ ስውር በነበረው ሰው ፊት ትንኮሣ ወይም ማነሳሳት  ይመስላል፣ ይልቁንም፣ ፈተና ነበር። ኢየሱስ በርጤሜዎስን በእውነት የሚፈልገው ምን እንደሆነ እየጠየቀው ነው፣ ለምንስ ጠየቀው? የዳዊት ልጅ ለአንተ ማን ነው? እናም ጌታ የዓይነ ስውራኑን ዓይንኖች መክፈት ይጀምራል። የውይይት መድረክ የሚሆነውን የዚህን ክስተት ሦስት ገጽታዎችን እንመልከት፡- ጩኸት፣ እምነት፣ ጉዞ።

በመጀመሪያ ደረጃ የበርጤሜዎስ ጩኸት፥ ይህም የእርዳታ ጥያቄ ብቻ አይደለም። የራሱ ማረጋገጫ ነው። ዓይነ ስውሩ “አለሁ፣ እዩኝ” እያለ ነው። አላይህም ኢየሱስ። አንተ ታየኛለህን?” አዎን፣ ኢየሱስ ለማኙን አይቶ በአካልና በልብ ጆሮ አዳምጦታል። ስለእራሳችን እናስብ፣ አንድ የእኔ ቢጤ (ለማኝ) ባለበት መንገድ ላይ ስናልፍ ወይም ስንሻገር፥ ስንት ጊዜ ነው ወደ ሌላ ቦታ አሻግረን የምንመለከተው፣ እርሱ የሌለ ይመስል ስንት ጊዜ ቸል እንላለን፣? እናም የለማኞችን ጩኸት እንሰማለን? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።

ሁለተኛው ነጥብ: እምነት የሚለው ነው። ኢየሱስ ምን ይላል? "'ኢየሱስም “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ'" (ማር 10፡52) በርጤሜዎስ እምነት ስለነበረው እና ስላመነ ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ያያል፥ ክርስቶስ የዓይኑ ብርሃን ነው። ጌታ በርጠሜዎስ እንዴት እንደሚመለከተው ተመልክቷል። ለማኝ ወይም የእኔ ቢጤ የሆነውን ሰው እንዴት ነው የምመለከተው? እሱን ችላ እላለሁ ወይ? እንደ ኢየሱስ ነው የምመለከተው? የእሱን ጥያቄ፣ የእርዳታ ጩኸቱን መረዳት እችላለሁን? ምጽዋት ስትሰጥ የለማኙን ዓይን ትመለከታለህን? ሥጋውን ለማዳመጥ በእጅህ ሰውነቱን ትነካለህ?

በመጨረሻም ጉዞው የሚለውን ቃል እናገኛለን። በርጤሜዎስ፣ ተፈወሰ፣ “በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ" (ማር. 10፡ 52)። ነገር ግን እያንዳንዳችን እንደ በርጤሜዎስ ነን፣ በውስጣችን ዓይነ ስውራን ነን፣ ኢየሱስን አንድ ጊዜ ወደ እኛ ከቀረበ በኋላ የምንከተለው እንደ በርጤሜዎስ የሆንን ሰዎች ነን። ወደ ድሃ ሰው ቀርበህ ቅርበትህን ስታሳውቅ፣ ያን ምስኪን ሰው መስሎ የሚቀርበው ኢየሱስ ነው። እባካችሁ ግራ እንዳንጋባ፡ ምጽዋት የሆነ ነገር መስጠት ብቻ ማለት አይደለም። ምጽዋትን አብዝቶ የሚቀበል ሰው ራሱን በጌታ ዓይን ስለሚያሳይ የሚሰጥ ነው።

መንገዳችንን በክርስቶስ ብርሃን ትጠብቅ ዘንድ የድኅነት ጎህ ወደ ሆነችው ማርያም አብረን እንጸልይ።

28 October 2024, 10:22

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >