የዛይድ ሽልማት ያሸነፉ አራት ሴቶች የዛይድ ሽልማት ያሸነፉ አራት ሴቶች 

ለሰላም የታገሉ አራት ሴቶች በአቡ ዳቢ ተገናኝተው ልምዳቸውን ማካፈላቸው ተገለጸ

ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት የዘንድሮን የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት አራት ሴቶች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በአቡ ዳቢ ተገናኝተው በመወያየት በፍትህ ዙሪያ ያከናወኗቸውን ሥራዎች እና ልምድ አካፍለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኔሊ፣ ሻምሳ፣ ላቲፋ እና ሚሼል የተባሉት አራቱ ሴቶች በዛሬው ማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ሚና ሲናገሩ፥ በንድፈ ሃሳብ ሳይሆን ከራሳቸው ልምድ በመነሳት በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጀመሩትን እና በዓለም ላይ የሚታወቁ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለማሳደግ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የዛይድ ሽልማት ለመቀበል የበቁት ሴት መሪዎች መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከል ፍትህ እና ሰላምንን ለማስፈን በከፈሉት መስዋዕትነት ጭምር እንደሆነ ታውቋል። ሽልማቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል ታይብ የተፈረመው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ታሪካዊ ሠነድ ፍሬ እንደሆነን ታውቋል።


በጥር 27/2016 ዓ. ም. በተካሄደው ዓመታዊ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ እነዚህ አራቱ ሴቶች በአቡ ዳቢ ተገናኝተው እያንዳንዳቸው የተጓዙበትን አስቸጋሪ መንገድ በዝርዝር ማካፈል የቻሉ ሲሆን፥ የሴት ልሂቃን ለሰው ልጅ ዕድገትን፣ ፍትህን፣ በአካባቢያዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማምጣት የሚያደርጉትን ልዩ ጥረት በጥልቀት መርምረዋል ።

በፈረንሣይ ሽብርተኝነትን ለማስወገድ ያደረጉት ጥረት

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2012 ዓ. ም. የደቡባዊ ፈረንሳይ ከተማ በሆነች ቱሉዝ ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት ሰለባ የሆነውን ልጇን የምታስታውሰው ላቲፋ ኢብን ዚያተን በልጇ ሞት ምክንያት ሐዘን ለመቀመጥ ጊዜ እንዳልነበር ገልጻ፥ ጥቃቱን የፈፀመው ግለሰብ ከድርጊቱ በኋላ በብዙ ወጣቶች ዘንድ እንደ ጀግና የሚቆጠር ሙስሊም አክራሪ እንደሆነ አስረድታለች። ላቲፋ እንደ እናት በሐዘን ብትጎዳም ነገር ግን በወጣቶች ምላሽ ግራ በመጋባት የኢማድ ማኅበርን በመመስረት የወጣቶች አክራሪነትን ለመከላከል መወሰኗን ገልጻለች።ማኅበሩ ባሁኑ በመላው አውሮፓ እያደገ የመጣ ሲሆን፥ ሰላምን ለማስፈን እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ከወጣቶች፣ ከቤተሰቦች እና ከማኅበረሰቦች ጋር በኅብረት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።


የፈረንሣይ ዜግነት ያላት ሞሮኳዊት ሙስሊም እናት ለሥራዋ ስኬታማነት ወሳኙ ሴት መሆኗ ብቻ ሳይሆን እናት በመሆንም ጭምር ሲሆን፥ እናቶች ፍቅርን ለሌሎች የሚያስተላልፉ፥ ጥቃትን እና ጦርነትን የማይፈልጉ መሆናቸው ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ ሴቶች በዓለም ውስጥ በሁሉም ቦታ የራሳቸው ቦታ እንዳላቸው አምናለሁ የምትለው ላቲፋ ኢብን ዚያተን፥ ዓለምን ከአንዳንድ ጥቃት ማዳን የሚችሉት ሴቶች ይሆናሉ በማለት በቁርጠኝነት ተናግራለች። በተጨማሪም ላቲፋ ኢብን ዚአተን በተልዕኮዋ ውስጥ በየቀኑ የምትመሰክረውን ነገር መሠረት በማድረግ ሴቶች በአካባቢያቸው የሚደርጓቸውን ጥረት አንድ እንዲያደርጉ በማለት ተማጽና፥ “የተለያየ ብቃት ያላቸው በርካታ ሴቶች ለዓለም እንደሚደርሱ እና የሴቶች ቁጥር አድጎ ኅብረታቸውን በማሳደግ የመሪነት ሥልጣን ባገኙ ቁጥር የበለጠ ሰላም ይኖረናል” ሲትም የጎርጎሮሳውያኑ 2021 ዓ. ም. የሰብዓዊ ወንድማማችነት የዛይድ ሽልማት አሸናፊ ላቲፋ ኢብን ዚያተን ሃሳቧን ገልጻለች።

የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ላቲፋ ኢብን ዚያተን
የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ላቲፋ ኢብን ዚያተን

ግጭቶችን የሚፈታ የሴትነት ስሜት

ከፈረንሳይ አሥራ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ እህት ኔሊ ሊዮን፥ የ 2024 ዓ. ም. የዛይድ ሽልማት ስላስገኘላት የሰብዓዊ ወንድማማችነት መመስከር ብቻ ሳይሆን፥ በቺሊ መዲና ሳንቲያጎ ውስጥ ነፃነታቸውን ከተነፈጉ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሴቶች መካከል የእውነተኛ እናትነት አገልግሎትን በማበርከት ላይ የምትገኘው የመልካሙ እረኛ ማኅበር አባል የሆነችው ገዳማዊት እህት ኔሊ ሊዮን፥ “ሙሄር ሌቫንታተ” የተሰኘ ፋውንዴሽን በማቋቋም የእስር ቅጣታቸውን የጨረሱ የሳንቲያጎ ከተማ ሴቶችን በመንከባከብ እና ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። 

እህት ኔሊ ሊዮን የምንኩስና ሕይወትን ለመኖር ባደረገችው ምርጫ ልጅ የመውለድ ዕድሏን ብትተወውም በሳንቲያጎ ከተማ በሚገኘው የሴቶች ማረሚያ ቤት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች "እናት" ተብላ ትጠራለች። እህት ኔሊ ፋውንዴሽኑ ከሚያደርገው የሥነ-ልቦና ድጋፍ በተጨማሪ አንዲት ሴት በተፈጥሮ በሚሰጣት ፍቅር አማካይነት መታደስ አስፈላጊ እንደሆነ ታረጋግጣለች። "የበለጠ ወንድማማችነት ያለበት ዓለምን ለመገንባት የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንገኛለን” የምትለው እህት ኔሊ፥ የሰው ልጅ የበለጠ በብርሃን እና በተስፋ የተሞላ እንዲሆን፣ ፍቅርን ያለ ልዩነት በማሳየት ምቾትን ለመስጠት እንደምትሠራ ገልጻለች።

የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት እህት ኔሊ ሊዮን
የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት እህት ኔሊ ሊዮን

ኬንያ ውስጥ ሰላምን ለማምጣት ውይይት የሚጫወተው ሚና

ኬንያ ውስጥ “ማማ ሻምሳ” በመባል በሁሉም ሰው ዘንድ የምትታወቀው ሻምሳ አቡበከር ፋድይል፥ በእናትነት ስሟ ኬንያ ውስጥ በሴቶች መካከል የአስታራቂነት ሥራን ጀምራለች። መጀመሪያ ላይ ሥራዋ በዋናነት የወጣት ወንጀለኛ ቡድኖችን ማፍረስ እና የሙያ ስልጠናን እንዲወስዱ ማድረግ ሲሆን፥ በዚህም ጥቃትን ከማድረስ እና ከፅንፈኝነት ውጪ ሌላ ዕድል የሌላቸው የሚመስሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እና ሕጻናት ሕይወት ለመታደግ ችላለች።

የሥራዋ ስኬት የኬንያ መንግሥትን፣ የሲቪል ማኅበራትን እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን መሪዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በኬንያ የሰላም እና የደኅንነት ብሔራዊ የሴቶች ተወካይ ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች። “ሴቶች ዘወትር ቤት ውስጥ በመሆናቸው ተዘንግተዋል” የምትለው “ማማ ሻምሳ” ግጭት ሲነሳ በጣም የሚጎዱት ሴቶች እንደሆኑ ገልጻለች።

ዛሬ እማማ ሻምሳ በግሏ በአገራዊ የማስታረቅ ስልቶች ውስጥ በመሳተፍ ሰላምን በማስፈን እና በማስቀጠል ውይይት ከቀን ወደ ቀን መሠራት ያለበት ሥራ መሆኑን እንድትገነዘብ አድርጓታል። “እንደ ሴቶች ውስጣዊ የትዕግስት ኃይል አለን፤ እግዚአብሔር ይህን ኃይል የሰጠን የትህትና እና የረዳትነት ችሎታ እንዲኖረን ነው” በማለት ተናግራ፥ ኃይላችን እናት መሆን እና እናትነትም ትልቅ ማዕረግ እንደሆነ አምናለሁ” ስትል አስረድታለች።

የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ሻምሳ አቡበከር ፋድይል ወይም  “እማማ ሻምሳ”
የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ሻምሳ አቡበከር ፋድይል ወይም “እማማ ሻምሳ”

የሄይቲ ፈር ቀዳጂዎች ውርስ መከተል

በሄይቲ ለመቶ ዓመታት የዘለቀውን የሴቶች ተሳትፎ ባህልን የምትከተለው የምጣኔ ሃብት ምሑር ሚሼል ፒዬር ሉዊስ ከፍተኛ ድህነት እና ብጥብጥ በነገሠባት አገሯ ሰላምን እና መረጋጋትን ለማስፈን በግሏ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ሚሼል ፒዬር ሉዊስ በማኅበራዊ ዕድገት ላይ ያላት ሰፊ ልምድ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2008 እስከ 2009 መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እንድትሠራ አስችሏታል።

ሚቼል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚመራውን እና “አልፋ ሚሽን” ተብሎ የሚታወቀውን ብሔራዊ የመሠረተ ትምህርት ፕሮጀክትን መርታለች። በኋላም በ1995 “ፎካል ፋውንዴሽን ፎር ኖውሌጅ አንድ ፍሪደም” የተሰኘ ተቋም አቋቁማ በትምህርት የማኅበረሰብ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የፆታ እኩልነትን እና ሌሎችንም ሥራዎች ስታበረታታ ቆይታለች። የዚህ ተቋም ስኬቶች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. የተዘጋጀውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት የዛይድ ሽልማት አሸናፊ እንድትሆን አድርጓታል።

በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1932 በካሪቢያን ደሴቶች የመጀመሪያውን የሴቶች ድርጅት ያቋቋሙትን ሄይቲያውያንን ያስታወሰችው ሚሼል ፒየር ሉዊስ፥ ፈር ቀዳጅነትን ከእነርሱ መማሯን ገልጻ፥ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን እና ጥቃቶችን ስትቃወም መቆየቷ ታውቋል።

የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ሚሼል ፒየር ሉዊስ፥
የዛይድ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ሚሼል ፒየር ሉዊስ፥

በአሁኑ ጊዜ ሄይቲ በተመሰቃቀለው ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ የገለጸችው ሚቸል ፒየር ሉዊስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሄይቲ ሰላም እንዲወርድ የሚያቀርቡት የማያቋርጥ የሰላም ጸሎት ውጤት እንደሚኖረው ያላትን ተስፋ ገልጻለች። መከላከያ በሌለው ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የግድያ ጥቃት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም በማሳሰብ፣ ኢፍትሃዊነትን በመቃወም ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን እና ሰብዓዊነትን በመደገፍ ሴቶች ትግላቸውን ሊቀጥሉ ይገባል” በማለት ንግግሯን ደምድማለች።

11 March 2024, 16:07